
ከጸኑት የጸናች፣ በጠላት ያልተደፈረች፣ ጠላቶቿን ሁሉ ድል የመታች፣ የገፏትን ሁሉ የጠላች፣ ጦር የመዘዙባትን፣ ጎራዴ የሳሉባትን ሁሉ ያንበረከከች፣ በልጆቿ ጀግንነት ለዘመናት በድል የተሞሸረች፣ በአሸናፊነት የተከበረች፣ በድል አድራጊነት የተረማመደች፣ በጠላቶቿ ፊት ግርማ እና ሞገስን ያገኘች፣ በወዳጆቿ የተወደደች፣ መመኪያ እና መኩሪያ የኾነች ጹኑ ሀገር።
ለግጭት የሰለሏት ያውቋታል፣ ጦር ያዘመቱባትን ድል አድርጋቸዋለችና ይረዷታል። ሲገፏት እየጣለቻቸው፣ ሲዘምቱባት እየገረሰሰቻቸው፣ በኀይሏ ድል እየመታቻቸው፣ የመጡበትን ጎዳና እያስጠፋችባቸው መልሳቸዋለችና ሳይወዱ በግዳቸው ያከብሯታል። እየራዱ እና እየተንቀጠቀጡ ይፈሯታል፣ የእጅ መንሻ እየያዙ ይመጡላታል፣ ፎክረው መጥተው አልቅሰው ይመለሱባታል፣ እየደነፉ ተነስተው እጅ ይነሱላታል።
ልጆቿ በነፃነት የኖረችውን፣ በክብር የሚውለበለበውን ሰንደቅ አስቀድመው ይገሰግሳሉ፣ ድል አድርገው በድል ይመለሳሉ። አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሰንደቅ በቀደመበት፣ የኢትዮጵያ ልጆች በዘመቱበት ሁሉ ድል አለ፣ በገሰገሱበት ሁሉ አሸናፊነት አለ። ያለ ድል የተመለሱበት ዘመን የላቸውም። ሰንደቁ የማይደፈር ነውና። ዘመናቸው በድል ያሸበረቀ፣ ታሪካቸው በአሸናፊነት የደመቀ ነው።
ኢትዮጵያ በነፃነት የኖረች፣ ለማንም በምንም ያልተደፈረች ሀገር ናት። ኢትዮጵያ በግፍ አትዘምትም፣ በግፍ የዘመቱባትንም አትታገስም። ጋራዋ አያረማምድም፣ ልጆቿም ስንዝር ሙሉ አያላውሱም። እርሷ ከሌሎቹ ትለያለች፣ ከሌሎቹም ትበልጣለች፣ ከሌሎቹም ተለይታ በረቀቀ ቀለም በታሪክ መዝገብ ላይ ሠፍራለች፣ ከሌሎችም ልቃ በማያረጅ ብራና ተቀርፃለች፣ በማይናወጽ ዓለት ላይ ተጽፋለች። ጥቁሮች ሁሉ እናታችን ይላሉ፣ ወራሪዎች ሁሉ ስሟን በሰሙ ጊዜ አንገታቸውን ይደፋሉ፣ ሽንፈታቸውን እያስታወሱ ይቆዝማሉ።
ዓለምን ያናወጸው የቅኝ ገዢዎች ክንድ አላናወፃትም የግፍ ግፍ የሠራው የፋሽሽት ሤራ አላንበረከካትም፣ ኀያላን ነን የሚሉት አመጽና ሁካታ አልሠበራትም፣ እርሷ ጽኑ ሀገር ናትና ጩኸት አይጥላትም፣ በዓለት ላይ የተመሠረተች ናትና ገፍተው አያናዉጿትም። ከተከበረችበት የክብር ዙፉን ላይ አያወርዷትም፣ እርሷ በፈተና ትጸናለች፣ በመከራ ትበረታለች፣ የማይቻል የሚመስለውን ትችላለች፣ ወዮላት አበቃች፣ ደቀቀች ስትባል ጠላቶቿን አድቅቃ ትነሳለች፣ ያጠፏታል የተባሉትን ሁሉ ታጠፋቸዋለች፣ ያንበረክኳታል የተባሉትን ሁሉ ታንበረክካቸዋለች፣ አይቻሉም የተባሉትን ሁሉ እንዳልነበር ታደርጋቸዋለች። ኢትዮጵያ ጀግኖችን የወለደች፣ በጀግኖቿም ስትጠበቅ የኖረች ታላቅ ሀገር ናት።
ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያን እና የኢጣልያን ጦርነት በከተቡበት መጽሐፋቸው ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ለሺህ ዓመታት ያህል የተደጋጋመ ሙከራ ተደርጓል። ኢትዮጵያውያን ግን ሀገራቸውን በሌላ በአድ ሳያሲዙ ባላቸው ኃይል ሲከላከሉ ቆይተዋል። በአውሮፓም ኾነ በኢሲያ ወይም በአፍሪካ የሚነሱ ታላላቅ መንግሥታት ጉልበት እያገኙ ግዛታቸውን በሚያሳፉበት ጊዜ ኢትዮጵያንም ለመደረብ ብዙ ጊዜ ሞክረዋል። ኢትዮጵያዊያን ግን ለማንም ሳይበገሩ እስካሁን ሀገራቸውን አስከብረው ቆይተዋል። ኢትዮጵያን አስገብሮ ለመያዝ በተደጋጋሚ የውጭ ጦር ቢመጣም ኢትዮጵያውያን ባላቸው ኀይል የማይበገሩ ኾነው የሚመጣውን የውጭ ጦር ሁሉ መልሰዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያን አበው እና እመው በጸሎታቸው፣ ጀግኖቹ በክንዳቸው፣ በላባቸው ፣በደማቸው ፣በአጥንታቸው ፣በከበረች ሕይወታቸው ሲጠብቋት ኖረዋል ፣ወደፊትም ይጠብቋታል።
ኢትዮጵያውያን ሀገር የሚጠብቀውን ጀግና ሠራዊት አብዝተው ይወዱታል። አበው በጸሎታቸው ሁሉ በዳር በድንበር ቆሞ ሀገር የሚጠብቀውን ጠብቅልን፣ አጽናልን፣ አበርታልን እያሉ ይጸልዩለታል። ኢትዮጵያውያንም በልባቸው ያስቡታል፣ በአንደበታቸው ያደንቁታል፣ አስተማማኝ ደጀን ይኾኑታል። ሀገራቸውን የሚጠብቅላቸው፣ ከጠላት የሚከላከላቸው፣ ሰንደቃቸውን በኩራት የሚያውለበልብላቸው፣ ከፍ ከፍም የሚያደርግላቸው ነውና እየቆረሱ ያጎርሱታል፣ እየቀዱ ያጠጡታል፣ ያስከብራቸዋልና ያከብሩታል።
የጸናች ሀገር ጀግና ወታደር አላት። የጸናች ሀገር ጽኑ ሕዝቦች አሏት። ከጠላት የሚከላከሏት፣ በመከራ ዘመን የሚያበረቷት፣ መከራውን የሚያሻግሯት፣ ጨለማውን የሚገፉላት፣ በብርሃንም የሚመሉላት። ወታደር ለኢትዮጵያ ከምንም ከማንም በላይ ነው። ወታደር ኢትዮጵያን ከአምላኳ ቀጥሎ ይጠብቃታል፣ ማንም እንዳይደፍራት ይከላከልላታል፣ በኢትዮጵያ ላይ በግፍ እግራችንን እናነሳለን ያሉትን ሁሉ ይቀጣላታል፣ እየቀጣም አደብ ያስይዝላታል።
የኢትዮጵያ ወታደር ጀግና ነው ጠላት የማይደፍረው፣ ብርቱ ነው መከራ የማይሰብረው። ጽኑ ነው እሾህና አሜካላ የማያስቆመው፣ ከግስጋሴው የማያስቀረው ኀያል ነው። የኢትዮጵያ ወታደር ኢትዮጵያውያን የወለዱት፣ ኢትዮጵያውያን የሚያከብሩት፣ ሰንደቃቸው እና ሀገራቸውን እንዲጠብቅላቸው አደራ የሰጡት ፣የሚመኩበት ፣የሚኮሩበት ነው።
በአንድነት የሚጠብቃቸው ፣በአንድነት ደጀን የሚኾኑት ፣ምልክቱ ሰንደቅ የኾነ፣ ሰንደቅ ማስከበር ፣ሀገር በክንዱ የሚያኖር ነው። ጀግናው ወታደር የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ነው።
የጽኑዋን ሀገር ጀግና ወታደር ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾኑ አፍሪካውያን ጭምር ይኮሩበታል። ይመኩበታል፣ በቸገራቸው ጊዜ ይጠሩታል፣ በጠሩትም ጊዜ ፈጥኖ ይደርስላቸዋል። ከጭንቅ እና ከችግር ይታደጋቸዋል። በክንዱ ብርታት ያበረታቸዋል። የጽኑ ሀገር ጀግና ወታደር፣ የጽኑ ሕዝብ ድንቅ መከታ፣ የታላቅ ሀገር ኀያል ወታደር። በደም እና በአጥንታችሁ ለዘመናት ሀገር ስትጠብቁ ለኖራችሁ፣ ጽኑ ሀገርንም ላወረሳችሁ፣ ዛሬም በደም እና በአጥንታችሁ ሀገር እየጠበቃችሁ ላላችሁ ሁሉ ክብር ይድረሳችሁ።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
