“ምድራዊ ፈተና በዝቶ፣ ዙሪያው ቢነድ በገሞራ፤ ጥሰን እናልፈዋለን፣ የማይሞት ታሪክ ልንሠራ።” የወታደሩ ዝማሬ

13

 

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በእሳት የተፈተነ እንደ ብረት የጠነከረ፣ በደሙ እና በአጥንቱ ክፋይ ሀርን ያቆመ፣ ዳር ድንበሯን እየጠበቀ ሉዓላዊነትን እያስከበረ፣ ኢትዮጵያን ከጠላቶቿ እየተከላከለ ለሕዝቦቿ የሁል ጊዜም መከታ እና ኩራት ነው።

“ከራስ በፊት ለሀገር” በሚለው መርሁ በዱር በገደሉ፣ በጋራ እና ሸንተረሩ፣ በቁር በሐሩሩ፣ በመራር መስዋዕትነት ሕይወቱን እየሰጠ ሕዝብ የሚያኖር፤ ሁሌም ኢትዮጵያን በህሊናው እያንሰላሰለ በመዝሙሩ ደጋግሞ እያሰበ፤ አደራውን እየተወጣ የሚኖር የሕዝብ አብራክ ክፋይ ነው።

“በደም አሻራሽ አትመው፣ ሕዝቦች ለሰጡን አደራ፤
ለሕገ መንግሥታችን ክብር ታጥቀን ቆመናል በጋራ።”… በሚለው የሠራዊቱ የመዝሙሩ ስንኝ ኢትዮጵያ የሰጠችውን የአደራ ቃል ኪዳን ጠብቆ ለእርሷ ሲል መድማቱን፤ አጥንቱን መከስከሱን፤ ሕይወቱን መስጠቱን፤ አያሌ መስዋዕትነትን መክፈሉን ይዘምራል።

በየዘመኑ ፈተና ቢገጥመውም እየጸና ለሀገር ያለውን እምነት አጽንቷል። በየዘመኑ የሚከሰቱ ፈተናዎችን በድል እየተወጣ የሉዓላዊነት እና የህልውና ዋስትና መኾን ችሏል።

“ባጎረስኩ ተነከስኩ” እንደሚባለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከአጠገቡ በነበሩት፣ ባሳደጋቸው አካላት ያበላበት እጁ ተክዶ ጥቃት የደረሰበት ዛሬ ጥቅምት 24 ስድስተኛ ዓመቱን ይዟል። ይህ ፈተናም የሠራዊቱ ታሪክ ኾኖ አልፏል። ነገር ግን ለእንደዚህ አይነቱ ፈተናዎች ሁሌም የማይበገር መኾኑን በመዝሙሩ ከፍ አድርጎ ያስተጋባል።

“ምድራዊ ፈተና በዝቶ፣ ዙሪያው ቢነድ በገሞራ፤
ጥሰን እናልፈዋለን፣ የማይሞት ታሪክ ልንሠራ።”

በሚለው የሠራዊቱ የመዝሙር ስንኝ ቀድሞ የተረዳ የደረሰበትን ሴራ በጣጥሶ በድል እያለፈ ዳግም ታሪክ ሠሪነቱን የወትሮ ዝግጁነቱን አረጋግጧል።

ሠራዊቱ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ከተጋረጠበት ፈተና፣ ከከፈለው መራር መስዋዕትነት ወጥቶ በእልህ እና ወኔ በብቃት ተደራጅቶ የጠላትን አከርካሪ የሰበረበት ጀግንነት የሚያስደንቅ ነበር። የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአንድ ወቅት “ሠራዊቱ በነበረው እልህ እና ወኔ አንዱ ወታደር እንደ አስር ኾኖ ተዋግቷል” በማለት ነበር የሠራዊቱን ጀግንነት የገለጹት።

ሠራዊቱ ለበርካታ ዓመታት አብሮት ለኖረው ታምኖ እንጂ እንኳንስ ለሕገ ወጡ ሕወሃት ቀርቶ ለማንም የማይጨበጥ መኾኑን ዳግም አስመስክሯል። ይህንን መጥፎ ታሪክ በወርቃማ አጋጣሚ ቀይሮ ወደ አዲስ ከፍታ መጓዝ ችሏል። በአጭር ጊዜ ውስጥ አደረጃጀቱን በማጠናከር፣ የጠላትን ስልት አክሽፎ ሀገሪቱን ከጠላት ሴራ ነጻ አድርጓል።

“የማንጨበጥ ነበልባል፣ እሳት ነን ለጠላታችን፤
ፍሙ ከርቀት ይፋጃል ብረት ያቀልጣል ክንዳችን”
የሚለውን የሠራዊቱን ብርታት እና ጀግንነት በተግባር አሳይቷል።

ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የጠላትን ሴራ ከሩቅ ማክሸፍ እና የሀገሪቱን ጂኦፖለቲካዊ ደኅንነት በዘመናዊ ሥርዓት ማስጠበቅ የሚችል ብቁ ተቋም ኾኗል። ከድሮን ቴክኖሎጂ እስከ ዘመናዊ ተዋጊ ጀቶች ባለቤት ለመኾንም በቅቷል። በፈጠረው አዲስ አቅም ጠላቶቹን እያሳፈረ የኢትዮጵያ አሸናፊነት ዘላለማዊ መኾኑን እያረጋገጠ ቀጥሏል።

“ከመሞት በላይ እንሙት፣ ደማችን ሺህ ጊዜ ይፍሰስ፤
አየር አፈሯ ይባረክ፣ ምን ጊዜም ስሟ ይታደስ።”
በማለት አንድ ሕይወቱን ለሀገሩ አሳልፎ ለመስጠት በገባው ቃል ኪዳን እያሰበ ኢትዮጵያን ሁሌም እየጠበቃት፤ እየሞተላት ዛሬም ዘልቋል።

#የመደመር_መንግሥት! #ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_24_2019_ዓ_ም

✍️በአሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ለውጭ ኀይሎች እና ለውስጥ ባንዳዎች ፍላጎት ማስፈጸሚያ አንኾንም” የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች