በሕዝብ የተመረጡ ተወካዮች ሕዝቡ ፈተናዎችን ተቋቁሞ የሰጣቸውን ድምጽ እና አደራ በተግባር ሊወጡ ይገባል።

6
ሀገራዊ ምርጫ ተካሂዶ አዲሱ መንግሥት በምሥረታ ሂደት ላይ በሚገኝበት በዚህ ወቅት በሕዝብ የተመረጡ ተወካዮች ሕዝቡ ፈተናዎችን ተቋቁሞ የሰጣቸውን ድምጽ እና አደራ በግልጽ እና በተግባር ሊወጡ እንደሚገባ በጅንካ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ምስክር ከተማ ተናግረዋል።
መምህሩ ኢትዮጵያ በጂኦፖለቲካዊ ጫናዎች እና በውስጥ ፈተናዎች አልፋ እዚህ ደረጃ መድረሷን ገልጸው የአዲሱ መንግሥት ቀዳሚ ተግባር የውስጥ ሰላምን እና ሕዝባዊ አንድነትን ማስጠበቅ ሊኾን እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተጨማሪም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያመጣቸውን ቁልፍ ውጤቶች እና የመፍትሔ ሃሳቦች በጥንቃቄ ወደ ተግባር መለወጥ የመንግሥት ዋነኛ የቤት ሥራ መኾን እንዳለበትም ጠቁመዋል።
አዲሱ መንግሥት ሲመሠረት የተመረጡ አካላት የፓርቲ ጉዳይ አስፈጻሚዎች ሳይኾኑ የሕዝብ ተወካዮች መኾናቸውን መገንዘብ አለባቸው ነው ያሉት።
መምህር ምስክር ተወካዮቹ ከሕዝብ ጋር ያላቸው ግንኙነት ወቅታዊ ብቻ ሳይኾን እስከ ቀበሌ እና ምርጫ ክልል ወርደው ሕዝቡን የሚያዳምጡበት እና ችግሩን አስቀድመው የሚፈቱበት ሊኾን እንደሚገባ መክረዋል።
የሀገርን ሰላም፣ አንድነት እና የኢኮኖሚ ጥንካሬን ለማረጋገጥ የመንግሥት ጥረት ብቻውን በቂ አለመኾኑን በመግለጽ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን እና ጋዜጠኞች ብሔራዊ ጥቅምን ከፖለቲካ አጀንዳ በመለየት ለሀገር ዕድገት በጋራ እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ዘላለም አስፋው
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሻብያ ሴራ እና የኢትዮጵያ የማይናወጥ ጽናት