
በሻብያ የሚመራው የኤርትራ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የዘመናት ግንኙነት በጥርጣሬ፣ በሴራ እና በተቃራኒ ጂኦፖለቲካዊ ፍላጎቶች የተሞላ ነው።
የኤርትራ መንግሥት በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ውስጥ የሚከተለው የውጭ ፖሊሲ የኢትዮጵያን ተጽዕኖ በመቀነስ እና በማዳከም ላይ የተመሠረተ ነው። ይህንን ዓላማ ለማሳካትም በርካታ የሴራ ስልቶችን ይጠቀማል።
ለአብነትም ከግብጽ ጋር የሚያደረገው ዘመናትን የተሻገረ ስትራቴጂካዊ ጥምረት አንዱ ነው። ግብጽ በዓባይ ወንዝ ላይ የብቸኝነት ተጠቃሚነት እና የበላይነትን የማስጠበቅ ፍላጎትን ዕውን ለማድረግም ኤርትራን ትጠቀምባታለች።
በዚህም በአስመራ እና በካይሮ መካከል የሚደረጉ ከፍተኛ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች የኢትዮጵያን ቀጣናዊ አቅም በማዳከም ላይ የተቃኙ የጋራ ዓላማ ናቸው።
በሌላ በኩል የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያን የውስጥ ሰላም ለማናጋት ልዩ ልዩ አማጽያንን በማሠልጠን፣ በማስታጠቅ፣ የሎጀስቲክስ እና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ረጅም ታሪክ አለው። ይህንንም የዓለም ዓቀፍ ተቋማት ያረጋገጡት ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራ እና ሶማሊያ ተከታታይ ኮሚቴ ይፋ ያደረገው የምርመራ ሪፖርት እንደሚጠቁመው ኤርትራ የኢትዮጵያን መንግሥት ለመውጋት የሚንቀሳቀሱ አማጺ ቡድኖችን በማስጠለል እና በማሠልጠን አለመረጋጋትን ስትፈጥር ቆይታለች።
በኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ጥሰት እና የድንበር ትንኮሳዎችም የዚሁ ሴራ አካል ናቸው። ዓለም አቀፉ የችግሮች አፈታት ቡድን (International Crisis Group) በየጊዜው በሚያወጧቸው ቀጣናዊ የደኅንነት ሪፖርቶች እንደተመላከተው በኤርትራ በኩል የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ትንኮሳዎች እና የውስጥ ጣልቃ ገብነቶች በተደጋጋሚ ተፈጽመዋል።
ነገር ግን “ድመት መልኩሳ አመሏን አትረሳ” የሚባለው አስተሳሰብ የተጠናወተው ሻብያ መሩ የኤርትራ መንግሥት ዛሬም ተመልሶ ከቀደመ ግብሩ ላይ ተቸክሏል። አንድነትን ትቶ ልዩነትን መርጧል፤ ሰላምን ገፍቶ ጦርነትን ሰብቋል፤ ልማትን ጠልቶ ጥፋትን ፈቅዷል፤ ወንድማማችነትን ረግጦ ጠላትነትን አውጇል።
ኢትዮጵያም የዓለም አቀፍ ሕግጋትን አክብራ፣ ሉዓላዊነቷን ታስከብራለች። ሕዝቧን አሰልፋ ሰላሟን ትጠብቃለች። የትናንት ታሪኳን ጠብቃ ዛሬን በመዋጀት ነገን ትቀጥላለች። ብሔራዊ ጥቅሟን አስጠብቃ ታስጠብቃለች። ዛሬም እንደ ትናንቱ በልጆቿ ታፍራ እና ተከብራ ትኖራለች።
በአሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
