
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዙር፣ 14ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 33ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ዘላቂነት ለማረጋገጥ የሰላም፣ የጸጥታ እና የልማት ሥራዎችን በውጤታማነት መፈጸም ወሳኝ መኾኑን አመላክተዋል።
በልማት ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም በአንድ እጅ ሰላምን በሌላ እጅ ደግሞ ልማትን ማስቀጠል እንደሚገባም ገልጸዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት በከተማዋ የተገኙ የሰላም እና የልማት ውጤቶችን መነሻ በማድረግ ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ የፈጠራ ሥራዎች እና ዕውቀት ጥቅም ላይ መዋላቸውን ነው የተናገሩት።
በቅንጅት የውስጥ ሰላምን በማረጋገጥ እና አዳዲስ አሠራሮችን በመዘርጋት በሁሉም ተቋማት መልካም ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም እና ነባሮችን በማጠናከር፣ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን እና የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በማከናወን ረገድ ውጤታማ ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት።
በከተማ ግብርና በተለይ የሌማት ቱፋትን ተግባራዊ ማድረግ፣ የደን ልማት እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራን ማስቀጠል፣ የበጋ መስኖ ስንዴ እና ሌሎች የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ሥራ በሰፊው ተከናውኗል ብለዋል።
ሕገ ወጥ ግንባታ እና የጎዳና ላይ ንግድን የመከላከል፣ በእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ሥራዎች ላይ የተሻለ ውጤት የማስመዝገብ፣ ከተማዋን መልሶ የማልማት፣ የማስዋብ፣ ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ምቹ የኢንቨስትመንት ምኅዳርን ለመፍጠርም በትኩረት መሠራቱን ጠቁመዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
