በአማራ ክልል ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የተገነቡ አምሥት የጤና ተቋማት በቅርቡ ይጠናቀቃሉ።

20
በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት እና የማኅበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችሉ ትልልቅ እና መካከለኛ የጤና ተቋማት ግንባታ መጀመራቸው ይታወሳል።
እነዚህን ተቋማት በታለመላቸው ጊዜ እና በጀት ለማጠናቀቅ ወደ ሥራ ይገባ እንጅ ፕሮጀክቶቹ በተለያዩ ምክንያቶች ሲጎተቱ እና አንዳንዶችም ተቋርጠው ቆይተዋል።
በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ያልተጠናቀቁ 17 ትልልቅ የጤና ተቋማትን በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መኾኑን በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጤና መሠረተ ልማት ዳይሬክተር ደርባባው ሽፈራው አስታውቀዋል።
ከ17ቱ ትልልቅ የጤና ተቋማት መካከል ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የተገነቡ ሦሥት ሆስፒታሎች እና ሁለት የሆስፒታል ማስፋፊያ ግንባታቸው በቅርብ ጊዜ እንደሚጠናቀቁ አስታውቀዋል።
በቅርቡ የሚጠናቀቁት አምሥቱ የጤና ተቋማትም ደብረማርቆስ ጠቅላላ ሆስፒታል፣ ፈለገሕይወት ኦፒዲ፣ የተፈራ ኃይሉ ሆስፒታል እናቶች እና ሕጻናት ማስፋፋፊያ፣ ግንደወይን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እና ግዳን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ናቸው።
እነዚህ የጤና ተቋማት ወደ ሥራ ሲገቡ የማኅበረሰቡን የረጅም ጊዜ የይገንባልን ጥያቄ የሚመልሱ፣ የብዙዎችን ሕይወት ለመታደግ የሚያስችሉ እና በሕክምናው ዘርፍ የሚገጥመውን የአገልግሎት ችግር በእጅጉ የሚያቃልሉ ናቸው ተብሏል።
ሌሎችም ተጀምረው የነበሩ በተለያዩ ምክንያቶች ያልተጠናቀቁ ትንንሽ እና መካከለኛ የጤና ተቋማት ግንባታዎችን አጠናቅቆ ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መኾኑ ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበፈተና የጸናው!
Next article“በአንድ እጅ ሰላምን በሌላ እጅ ደግሞ ልማትን ማስቀጠል ይገባል” አቶ ጎሹ እንዳላማው