በፈተና የጸናው!

14
ኢትዮጵያዊ ማንነትን፤ የዓድዋ ጀግንነትን እና ሕዝባዊነትን ተላብሶ ሕዝብን ሲጠብቅ እና ከክፉ ሲከላከል ይታወቃል። ለጠማው የውኃ ኮዳውን ቀንሶ አጠጥቶ፤ ያለውን ደረቅ ብስኩት አካፍሎ ፍቅር መስጠትም መገለጫው ነው፤ ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት።
ኢትዮጵያዊ ወታደር ወገኑ ሲጠቃ ከመድረስ አልፎ ወደ ጎረቤት ተሻግሮ ማንነቱን አሳይቷል፤ እሱነቱንም አስመስክሯል። ይህ ሠራዊት ታዲያ በ2013 ዓ.ም ከ20 ዓመት በላይ ሕዝብን እየጠበቀ በተቀመጠበት አካባቢ አንድ ተፈጥሯዊ ክስተት ተከሰተ። ወቅቱ ሰብል የሚደርስበት
ነበርና ሰብልን ሊያጠፋ የሚችል የአንበጣ መንጋ ሲከሰት ይህን ችግር ከማኅበረሰቡ ጋር ለመከላከል ተሰማራ፤ ከሕዝብ ጋር ተሰልፎም ላቡን እየጠረገ ሲከላከል ዋለ። ይህ የሕዝብ አጋዥ እና ጠባቂ ሠራዊት ግን ምሽት ላይ ደክሞት ባረፈበት ቅጽበት እናጠፋዋለን ብለው ያሰቡ ጠላቶቹ
ተነሱ፤ ከጀርባውም ወጉት፤ ይህ ግን የሕዝብ ጋሻ ከመኾን አላገደውም፤ ይበልጡን አጠነከረው እንጅ። በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ይህ ድርጊት ታዲያ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ከባድ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ነው። መከላከያ ሠራዊት በችግሮች እየጠነከረ እና ይበልጡን እየዘመነ
የሚሄድ መኾኑን በተግባር ያሳየ ሠራዊትም ነው። ለዚህም ማሳያው ይፈርሳል ብለው የወጉት አሁን ላይ በዘመናዊ ትጥቅ ደርጅቶ ከሀገር ውስጥ እስከ ባሕር ማዶ የሚነገርለት እና ጥንካሬው የሚነሳለት ሠራዊት መኾኑን ቀጥሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለሕዝብ
ተወካዮች ምክር ቤት ስለሠራዊቱ ሕዝባዊነት እና ደጀንነት ሲናገሩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከራሱ አልፎ ለሀገር ሕልውና እና ክብር ቅድሚያ የሚሰጥ፤ በፈተና ውስጥ አልፎ ሉዓላዊነትን በጽናት ያስከበረ አስተማማኝ ኀይል መኾኑን ገልጸዋል። ሠራዊቱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የተላበሰ፣
ከማንኛውም የፓርቲ እና የብሔር ፖለቲካ የጸዳ፣ በሙያዊ ብቃት እና በሀገራዊ ፍቅር ብቻ የቆመ ተቋም እንዲኾን የተሠራው ሥራ የሀገርን ደኅንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ያስቻለ ትልቅ ምዕራፍ መኾኑን ተናግረዋል።
👉 በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበሰሜን ጎንደር ዞን በሰላም እጦት ምክንያት የተቋረጡ የፌዴራል መንገድ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ምን እየተሠራ ነው?
Next articleበአማራ ክልል ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የተገነቡ አምሥት የጤና ተቋማት በቅርቡ ይጠናቀቃሉ።