
ኢትዮጵያ ወደ ዕድገት ጎዳና ያመራች ሲመስላቸው የሚነሱ ጠላቶች ያሉባት ሀገር መኾኗ የታወቀ ነው። ታዲያ ዕድገቷን የሚያረጋግጡ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ስታጠናቅቅ እና አዳዲስ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ስትጀምር ስጋቶችን ቀድሞ የሚመክት ዋስትና ሊኖራት ግድ ነው።
በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ የጸጥታ ተቋማቷ ላይ የለውጥ ሥራ ሠራች። የለውጥ ሥራው ስብራቶችን በመጠገን ብቻ ሳይገደብ የተቋማቱን የመዋቅር ስብጥር፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሀብት፣ የሠለጠነ የሰው ኀይል እና ሁለንተናዊ ዝግጁነትን በብዙ እጥፍ በማሳደግ ረገድ ታሪካዊ ለውጥ ነው ማከናወን የቻለችው።
ሀገሪቱ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር እና የብሔራዊ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አቅምንም በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጋለች። ይህ መዋቅራዊ ሽግግር የተራቀቁ የሳይበር ጥቃቶችን በማክሸፍ የዲጂታል ሉዓላዊነቷን የማስከበር ሙሉ ብቃት አቀዳጅቷታል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ራሱን በዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች፣ ድሮኖች እና ራዳሮች በመገንባት የአየር እና የምድር መከላከያ አቅሙን አዘምኗል። የሀገር ውስጥ የመከላከያ ኢንደስትሪዎችን በማዘመን የትጥቅ ጥገኝነትን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ ደግሞ ስኬቱን አጉልቶታል።
በብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት የተገነባው የተራቀቀ የመረጃ ትንተና ብቃትም ሌላው የለውጥ ሥራው ፍሬ የታየበት ተቋም ነው።
ይህ የደኅንነት እና የጸጥታ ተቋማት ተቋማዊ ጥንካሬ የሀገርን ሰላም ከማስከበር ባለፈ በቀጣናው የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖችን ቀድሞ በመምታት የጂኦ- ፖለቲካዊ መረጋጋት ዋነኛ ምሰሶ መኾኑን በተግባር አስመስክሯል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአንድ ወቅት ሲናገሩ ዛሬ ሀገራችን በልጆቿ ዕውቀት እና አቅም በራሷ መከላከያ ኢንዱስትሪዎቿ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን፣ ተተኳሽ ጥይቶችን እና ሌሎች ዘመናዊ መሣሪያዎችን ማምረት ችላለች ብለዋል።
ይህ ስልታዊ ራስን መቻል ለሕዝብ ሰላም እና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጠንካራ መሠረት መኾኑንም ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት የተመዘገበው ሥር-ነቀል የተቋማት ሪፎርም ኢትዮጵያን በፈተናዎች መሐል የማይናወጥ ታሪካዊ የጥንካሬ ማማ ላይ ሰቅሏታል።
ዛሬ የኢትዮጵያ የደኅንነት እና የጸጥታ ተቋማት የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኩራት እና የማይደፈር የሀገር ሉዓላዊነት ጋሻ ናቸው። ሀገሪቱ አሁንም ኾነ ወደፊት የሚቃጡባትን ማናቸውንም ዓይነት ጥቃቶች ቀድማ የመከላከል አቅሟን በየቀኑ እያሳደገች የሰላምና የልማት ጉዞዋን በጽናት ትቀጥላለች።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
