
ዋቢ የምግብ ኮምፕሌክስ በደብረብርሃን ከተማ በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስገነባውን የፋብሪካ በማጠናቀቅ አልሚ ምግብ እና ዱቄት ማምረት ጀምሯል።
የከተማ አሥተዳደሩ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ብርሃን ገብረ ሕይወት እንደገለጹት ባለፉት ሦሥት ዓመታት በ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ 58 ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት በመግባታቸው ለ7 ሺህ 800 በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
ዛሬ ሥራ የጀመረው ዋቢ የምግብ ኮምፕሌክስም ለ111 ዜጎች ቀጥተኛ የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲኾን በተያዘው በጀት ዓመት ተጨማሪ 30 ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ታቅዶ እየተሠራ ነው።
የዋቢ የምግብ ኮምፕሌክስ የሕግ አማካሪ ደመላሽ ጌታቸው ፋብሪካው ሀገርን በምግብ ራስን የማስቻል ጥረትን እንደሚያግዝ ገልጸው በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ የሥራ ዕድል ፈጠራውን እስከ 300 እንደሚያደርስ ጠቁመዋል።
የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ደብረብርሃን ለኢንቨስትመንት ምቹ እና ሰላማዊ መኾኗን ገልጸው አሥተዳደሩ በቂ የመሬት አቅርቦት፣ የሠለጠነ የሰው ኀይል እና ቀልጣፋ አሠራር በማዘጋጀት ባለሃብቶችን ለመቀበል እና ማነቆዎችን ለመፍታት ዝግጁ መኾኑን አረጋግጠዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የክልል እና የከተማ አሥተዳደሩ ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ዮናስ ታደሰ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
