በደብረ ብርሃን በሳምንት እስከ 100 ሕሙማንን ማስተናገድ የሚችል የኩላሊት እጥበት ማዕከል ተከፈተ።

8
በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር፣ በሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ፣ በሄዋን ፋውንዴሽን እና በቶም ልዩ የኩላሊት ሕክምና ትብብር የተገነባ አዲስ የኩላሊት እጥበት ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
በ5 የኩላሊት እጥበት ማሽኖች የተደራጀው ይህ ማዕከል በሳምንት እስከ 100 ሕሙማንን ማስተናገድ የሚያስችል አቅም አለው።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት እና የከተማው ጤና መምሪያ ኀላፊ በቀለ ገብሬ የማዕከሉ መከፈት ለደብረ ብርሃን፣ ለሰሜን ሸዋ እና ለምሥራቅ አማራ አካባቢዎች ከፍተኛ የሕክምና ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
በቀጣይም ደረጃውን የጠበቀ እና ዘላቂ አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል ለመገንባት በትኩረት እንደሚሠራም ነው ያረጋገጡት።
የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መሥራች እና ዋና ሥራ አሥኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ እና የምክትል ቦርድ ሠብሣቢው ሳላሃዲን ከሊፋ በበኩላቸው የመንግሥት እና የባለሃብቱ ቅንጅት ለዚህ ስኬት ማብቃቱን በመጥቀስ ማዕከሉ በተለይም የገጠሩን ማኅበረሰብ ሕይወት ለመታደግ እና የጤና ሽፋን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ የኩላሊት እጥበት ሕክምና ከፍተኛ የተደራሽነት ችግር ያለበት መኾኑን አንስተው ማዕከሉ ለዓመታት ወረፋ ሲጠብቁ የነበሩ ወገኖችን ሕይወት የሚታደግ፣ የሪፈር እንግልትን የሚቀንስ እና የሀገሪቱን የጤና ፖሊሲ የሚደግፍ መኾኑን ገልጸዋል።
አክለውም በጤናው ዘርፍ አርዓያነት ያለው የበጎ አድራጎት ተግባር ላሳዩ አካላት በሙሉ ምሥጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ዮናስ ታደሰ
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የአጀንዳ ርክክቡ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሀገራዊ ፈተናዎች በሰላማዊ ምክክር ለመፍታት ያለንን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋገጠ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleበ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የተገነባውን የምግብ ፋብሪካ ወደ ምርት ገባ።