
ኢሬቻ የምስጋና፣ የሰላም፣ የፍቅር እንዲሁም የእርቅ በዓል ነው። በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየው ይህ ባህላዊ ትውፊት፣ ክረምቱ አልፎ መስከረም ሲጠባ “መልካም ጊዜ ስላሳየኸን፣ ከዝናቡና ከጎርፉ ጠብቀህ ለብርሃን ስላበቃኸን” ተብሎ ፈጣሪ የሚመሰገንበትም ነው።
የኢሬቻ በዓል ከምስጋና በዓልነቱ ባሻገር የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህላዊ አልባሳትና ውበቶች የሚንጸባረቁበት ነው።
በዓሉ የኢትዮጵያን የባህል ብዝሃነትና ውበት በአንድ ላይ አጣጥሞ የሚያሳይ እውነተኛ ኅብረ-ቀለም ነው።
በኢሬቻ አከባበር ወቅት ቂም ይረሳል፤ ሰላምና ወንድማማችነት ይበሰራል። ሕዝቡ ወደ ወንዞችና ሐይቆች በመሄድ እርጥብ ሳር፣ አለንጌ እና ቦኩ ይዞ አምላክን በማመስገን በተፈጥሮና በሰው ልጅ መካከል ያለውን ጠንካራ ቁርኝት ያሳያል።
በአባ ገዳዎች እና በሀደ ሲንቄዎች በሚመራው በዚህ ሥርዓት ላይ ባህላዊ ዘፈኖችና ጭፈራዎች የበዓሉን ድምቀት የበለጠ ያጎሉታል።
የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ሕዝብ ባህላዊ እሴት ከመሆኑም በላይ፣ የኢትዮጵያውያንን አንድነትና ኅብረ-ቀለም በግልጽ የሚያሳይ የጋራ መድረክም ነው።
