የግብጽ የውኃ ፖለቲካ፣ የሀሰት ትርክቶች እና በኢትዮጵያ ላይ እየሠራች ያለችው ሴራ

9

 

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን የመጠቀም መብቷን ተጠቅማ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን መገንባት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በዋናነት ያተኮረው በዲፕሎማሲያዊ ጫና፣ በሀሰት ትርክቶች እና የኢትዮጵያን ውስጣዊ ትኩረት ለመቀልበስ በመሞከር ላይ የተመሠረተ ነው።

ለዚህ እውነታ ማረጋገጫው በተለያዩ ጊዜያት የምታደርጋቸው የሀሰት ውንጀላዎች እና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማደናገሪያዎች ናቸው።

ግብጽ በዓለም አቀፍ መድረኮች የምታቀርበው ኢትዮጵያ የዓባይ ውኃ ብቻዋን ልትጠቀም ነው፤ የውኃ እጥረት ይፈጥርብኛል የሚለው ስጋት ሳይንሳዊ መሠረት የሌለው እና የፖለቲካ ማደናገሪያ ነው። ይህንንም የውኃ ፖለቲካ ከፍተኛ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ “ኢትዮጵያ እና ዓባይ፡ የሀገር ውስጥ እና ቀጣናዊ የሃይድሮ ፖለቲካ አሻሚ እውነታዎች” በተሰኘ መጽሐፋቸው ግብጽ ለዘመናት የያዘችው የውኃ ፖሊሲ ላይ የተመሠረተው በብቸኝነት እና በበላይነት የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት ያስረዳሉ። ግብጽ ታሪካዊ መብት በሚል የምታቀርበው ውንጀላ ኢትዮጵያን እንደ ሕገወጥ አድርጎ ለማቅረብ የተሠራ የዲፕሎማሲ ስልት እንጂ ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀምን ያማከለ አይደለም ይላሉ።

ግብጽ የውኃ ፖለቲካ ግቧን ለማሳካት የኢትዮጵያ ውስጣዊ ፖለቲካ፣ ብሔር ተኮር እና ማኅበራዊ ውጥረቶች ባጋጠሟት ቁጥር የነገሮችን መባባስ እንደ መልካም አጋጣሚ ስትጠቀምበትም ቆይታለች። አሁንም ይህንኑ ተግባር በእጅ አዙር ለመቀጠል እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች።

በምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ላይ ጥናት ያደረጉት አሌክስ ዲ ዋል ‘ም “የአፍሪካ ቀንድ እውነተኛ ፖለቲካ፡ ገንዘብ፣ ጦርነት እና የድርድር ንግድ” በተሰኘው መጽሐፋቸው በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል የሚደረግ የኀይል ሚዛን ፍልሚያ አብዛኛውን ጊዜ በወኪሎች እንደሚከናወን ይገልጻሉ።

ግብጽ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚነሱ አለመግባባቶችን እና ብሔር ተኮር ውጥረቶችን በገንዘብ፣ በሚዲያ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በማጠናከር የኢትዮጵያን ትኩረት ከልማት እና ከግድቡ ሥራ ለመቀልበስ ስትጠቀምበት እንደነበር ያብራራሉ።

አምባሳደር ዘነበ ከበደ የግብጽ ታሪካዊ ስትራቴጂ ኢትዮጵያ በምንም አይነት መልኩ ጠንካራ እና የተረጋጋ መንግሥት እንዳይኖራት ማድረግ ነው። ኢትዮጵያ በውስጣዊ ግጭት እና በኢኮኖሚ ድህነት ውስጥ ስትቆይ የዓባይን ተፋሰስ ለማልማት አቅም አይኖራትም በሚል እምነት ግብጽ የኢትዮጵያን ውስጣዊ ክፍተቶች ስትጠቀም ቆይታለች። አሁንም ይህን የቆየ ስትራቴጂ ለመጠቀም እየሞከረች ትገኛለች ይላሉ።

በምሁራኑ ጥናት መሠረት የግብጽን የሀሰት ውንጀላ እና ጣልቃ ገብነት ለመመከት ከኢትዮጵያ የሚጠበቁ ስትራቴጅያዊ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ። አንደኛው እርምጃ ሳይንሳዊ እና እውነታን መሠረት ያደረገ ዲፕሎማሲ ነው። የታላቁ ሕዳሴ ግድቡ በታችኞቹ ሀገራት ላይ ጉዳት እንደማያደርስ በሳይንሳዊ መረጃዎች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቅ ያስፈልጋል።

ፍትሐዊ የመልማት መብትን ማስከበርም ሌላው እርምጃ ነው። የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የትብብር እና የፍትሐዊ አጠቃቀም ማዕቀፍ እንዲጸድቅ እና ሥራ ላይ እንዲውል ማድረግም ይጠበቃል። የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን ለመመከት ትልቁ መሳሪያ የሀገር ውስጥ ፖለቲካዊ መረጋጋት እና ብሔራዊ አንድነት ነው። ስለዚህ ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር ያስፈልጋል ይላሉ።

💬 በእነዚህ ምሁራዊ እውነታዎች እና በግብጽ የሀሰተኛ የዲፕሎማሲ አካሄድ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው? ሃሳብዎን ያካፍሉን!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!

#አሚኮ #የኢትዮጵያ_ዲፕሎማሲ🇪🇹​

#ባሕር_ዳር #መስከረም_23_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ሮዛ የሻነህ

‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleሀገርን በማስቀደም ለሀገር ጥቅም እና አንድነት በጋራ እንሠራለን።
Next articleየሥነ-ሥርዓት ሕጉን በትክክል መተግበር ለፍትሕ አሥተዳደሩ ውጤታማነት ወሳኝ ነው።