
«የዳኝነት ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ» በሚል መሪ መልዕክት ከመስከረም 20/2019 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ በሰነበተው የክልሉ ዳኞች 2ኛው ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ለአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች በፍትሐብሔር እና በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ዙሪያ ገለጻ እና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በመድረኩ ገለጻ ያቀረቡት የሕግ አማካሪው መንበረፀሐይ ታደሰ (ዶ.ር) የፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ በፍትሕ አሥተዳደሩ ፍጥነት፣ ወጪ፣ ቀላልነት እና ፍትሐዊነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለው በመኾኑ፤ የሕጉ ይዘት ብቻ ሳይኾን በተግባር የሚፈጸምበት መንገድ ለፍትሕ ውጤታማነት ወሳኝ መኾኑን አብራርተዋል።
በፍትሕ አሥተዳደሩ የሚነሱ ቅሬታዎች በአብዛኛው ከሥነ-ሥርዓት ሕግ አፈጻጸም ድክመት የሚመነጩ መኾናቸውን የጠቆሙት ዶክተር መንበረፀሐይ የዳኞች ገለልተኝነት ከሂደቱ መራቅ ሳይኾን ሂደቱን በሕግ እና በማስረጃ መሠረት በንቃት መምራት ነው ብለዋል።
የቀረቡ ማስረጃዎችን በትክክል በመመዘን በግልጽና በተጨባጭ ምክንያት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ማስተላለፍ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በሕጉ እና በአፈጻጸሙ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ዳኞች በየዕለቱ የሕግ ዕውቀታቸውን ማሳደግ እና የሥነ-ሥርዓት ሕጉን በጥልቀት መረዳት እንዳለባቸውም ነው ያብራሩት።
በመርሐ ግብሩ ማጠናቀቂያ ከተሳታፊ ዳኞች ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች በአቅራቢው ምላሽ እና ተጨማሪ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
#አሚኮ #ፍትሕ_አማራክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_23_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
