“አልሚዎችን ለመሳብ እና ኢንቨስትመንትን ለማስፋት የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት ወሳኝ ጉዳይ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

9
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በአማራ ክልል የሚያጋጥሙ የኀይል አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ ኀላፊዎች ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ
ኀላፊ እንድሪስ አብዱ የአምራች ኢንዱስትሪው ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱን አንስተዋል። በክልሉ በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል። የኢንዱሰትሪዎች የማምረት አቅም 65 በመቶ መድረሱንም ተናግረዋል። ከነበረበት አንጻር ለውጥ ቢኖርም የኀይል
አቅርቦት ችግሩ በሚፈለገው ልክ እንዳያመርቱ አድርጓል ነው ያሉት።በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የውጭ ምንዛሬ ግኝት እያደገ ነው ብለዋል። ዘርፉ ላይ ተስፋ ሰጪ እድገት እየታየ ነው ያሉት ኀላፊው ተስፋውን የበለጠ ለማሳደግ እና ውጤታማ ለማድረግ
የኀይል አቅርቦት ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል። በክልሉ የሴብስቴሽን ከፍተኛ ጭነት እና ተጨማሪ ፍላጎት መሸከም አለመቻል፣ የኀይል መቋረጥ እና የቮልቴጅ መዋዠቅ፣ የትራንስፎርመር እና የሦሥት ፌዝ ቆጣሪ እጥረት፣ የኤሌክትሪክ መስመር እና የሰብስቴሽን ግንባታ መጓተት እንዲሁም ሌሎች
ችግሮች እንዳሉ ገልጸዋል። እነዚህ ችግሮች ደግሞ በኢንዱስትሪዎች ላይ የምርት መቀነስ፣ የማሽን ጉዳት፣ የምርት ጥራት መቀነስ፣ የገበያ ዋጋ፣ የኢንቨስትመንት ፍስሰት እንዲዳከም እና የሠራተኞች ምርታማነት እንዲቀንስ አድርጓል ነው ያሉት። በክልሉ ያለው የኢንቨስትመንት ፍላጎት እና
የመብራት ኀይል አቅርቦት እንዳልተመጣጠነም ገልጸዋል።ወደፊት አነስተኛ አቅም ያላቸውን ሰብስቴሽኖችን አቅም ማሳደግ እና የተጀመሩትን የሰብስቴሽን ግንባታዎች ማፋጠን እንደሚገባም አመላክተዋል። ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ራሳቸውን የቻለ የኀይል አቅርቦት እንዲኖራቸው ማድረግ
እንደሚገባም አስገንዝበዋል።የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በቅንጅት በመሥራት ችግሮችን መፍታት አለብን ብለዋል። ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት ሲመጡ አቅማቸውን እና የሚያስፈልጋቸውን የኀይል አቅርቦት ለኤሌክትሪክ ኀይል ማሳወቅ
እንደሚገባም ተናግረዋል። ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ የኀይል አቅርቦት መጠየቅ የግለሰቦችንም ኾነ የሀገርን ሃብት ይጎዳል ነው ያሉት።
በየቦታው የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ መኾናቸውንም አመላክተዋል።በአማራ ክልል ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ 13
የኤሌክትሪክ ኀይል ፕሮጄክቶች እንዳሉም ተመላክቷል። በታወር ላይ የሚከሰት ስርቆርትን፣ የወሰን ማስከበር ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ተገልጿል።የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉ መንግሥት አልሚዎችን ወደ ክልሉ እየሳበ መኾኑን ገልጸዋል። ባለሀብቶችን
ለመሳብ እና ኢንቨስትመንትን ለማስፋት ደግሞ የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት ወሳኝ ጉዳይ መኾኑን ተናግረዋል።በኀይል አቅርቦት እጥረት ብቻ ወደ ሥራ መግባት ያልቻሉ እና በሙሉ አቅማቸው ማምረት የማይችሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውንም አንስተዋል። አምራች ኢንዱስትሪውን
ውጤታማ ለማድረግ የኀይል አቅርቦት ችግርን መፍታት ይገባልም ነው ያሉት።የክልሉ መንግሥት መፍታት የሚገባውን ችግር እንደሚፈታም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይልም መፍታት የሚገባው ችግር አለ፤ ችግሮችን በቅንጅት በመፍታት በግንባታ ላይ የሚገኙትን ወደ ሥራ
ማስገባት አለብን ነው ያሉት።በመወያየት እና ለእያንዳንዱ ሰው ኀላፊነት በመስጠት ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የኃይል አቅርቦት ለአብዛኛዎቹ የልማት ሥራዎች አንቀሳቃሽ ሞተር ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ