ሀገርን በማስቀደም ለሀገር ጥቅም እና አንድነት በጋራ እንሠራለን።

7

 

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር በሀገራዊ የሰላም እና የልማት ጉዳዮች ዙሪያ ከሃይማኖት አባቶች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ጽሕፈት ቤት የኢኮኖሚ አማካሪ አስናቀ ይርጉ የሃይማኖት አባቶች ሀገርን ከነክብሯ ለማሻገር፣ ለሕዝብ ሰላም እና ጥቅም በመቆም ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የማኅበረሰቡን መልካም እሴቶች የሚጥሱ አካሄዶችን የሃይማኖት አባቶች በመገሠጽ ለሰላም መረጋገጥ በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ስለሺ ተመስገን አባቶች በየሃይማኖት ተቋማቱ ሰላምን በመስበክ ሀገራዊ እሴቶች ጸንተው እንዲቀጥሉ ሃይማኖታዊ ተልዕኳቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በየጊዜው የሚፈጠሩ ግጭቶች እና አለመግባባቶች በሰላም ተፈተው ውስጣዊ አንድነት እንዲጠናከር ስለ ሰው ልጅ ክብር፣ እኩልነት፣ ፍትሕ እና መከባበር በመቆም ለሀገር አንድነት መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በምክክሩ የተሳተፉት የሃይማኖት አባቶች ሃይማኖታዊ እሴቶችን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ ሀገርን በማስቀደም ለሀገር ጥቅምና አንድነት በጋራ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

መንግሥት በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በማስተዋል እና በጥበብ እንዲፈታም ጠይቀዋል።

መሪዎችን በመምከር እና በመገሠጽ ለሀገር ሰላም፣ ፍትሕ እና ሀገራዊ አንድነት መረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!

#አሚኮ #ሰላም_ደብረማርቆስ_ኢትዮጵያ🇪🇹​

#ደብረ_ማርቆስ #መስከረም_23_2019_ዓ.ም

‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleሰላም የሁሉም ሃይማኖቶች መሠረት ነው።
Next articleየግብጽ የውኃ ፖለቲካ፣ የሀሰት ትርክቶች እና በኢትዮጵያ ላይ እየሠራች ያለችው ሴራ