
የዛሬይቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትናንት ከነበረበት የውጊያ ታሪክ እና አውድ ጋር ሲነጻጸር በዘመናዊነት የታነጸ የብቃት ከፍታ ላይ የሚገኝ ነው። ሠራዊቱ አሁን የያዘው ቁመና አርቆ አሳቢነትን፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን እና ስልታዊ ብቃትን ያቀናጀ የሥልጡን ኃይል ማሳያ ነው።
ሠራዊቱ ዓለም የደረሰባቸውን የጦር መሣሪያዎች እና ቴክኖሎጂዎች ታጥቆ ይገኛል። ከዚህም በላይ ችግሮች አደጋ ከመፍጠራቸው በፊት ቀድሞ የመተንበይ ብቃቱ እጅግ የላቀ ነው። ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን እና የክትትል ሥርዓቶችን በመጠቀም አደጋዎችን ከምንጩ ማክሸፍ እና ሰላምን
ማረጋገጥ የዕለት ከዕለት አሠራሩ ኾኗል። የሠለጠነ አዕምሮን እና የዘመኑን ዕውቀት ከዘመን ሠራሹ የጦር መሣሪያ ጋር ማቀናጀት መቻሉ ደግሞ ሠራዊቱ በማንኛውም መልክ እና የውጊያ አውድ ውስጥ ሁሌም የበላይነትን እንዲይዝ አስችሎታል። ይህ ሁሉ ቴክኖሎጂ እና ስልታዊ ዝግጁነት
በባዶ ወረቀት ላይ የተጻፈ ንድፈ-ሃሳብ አይደለም፤ ባለፉት ዓመታት በፈተና ውስጥ አልፎ በተግባር የተፈተነ እውነት እንጂ። ኢትዮጵያን ለመበተን የተነሱ የውስጥም ኾነ የውጭ ጠላቶች ያጋጠሟቸው መራራ ሽንፈቶች የዚህ አዲስ የቁመና ለውጥ ሕያው ምስክሮች ናቸው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዛሬ የደረሰበት ቁመና የትናንት አኩሪ ታሪኩን ከዘመናዊው የቴክኖሎጂ ዓለም ጋር አቆራኝቶ የቀጠለ የድል ምዕራፍ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የጦር ኀይላችን የሪፎርም እና የዘመናዊነት ጉዞ የሀገርን ህልውና የማስከበር ዋስትና ብቻ
ሳይኾን የቀጣናውን ሰላም ዘላቂ የሚያደርግ አቅም ጭምር ገንብቷል ማለታቸው ይታወሳል። ሀገራዊ ሉዓላዊነታችንን የሚደፍር ማንኛውንም ኀይል ለመመከት የሚያስችል አቅም ገንብተናል፤ ሰማያችንም ኾነ ምድራችን በቁጥጥራችን ስር ነው ብለዋል። የሠራዊታችን ቁመናም የኢትዮጵያን
ታላቅነት እና ጽናት የሚያንጸባርቅ ነው ሲሉም ገልጸዋል። የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባንድ ወቅት እንደተናገሩት የሠራዊቱ የሪፎርም ሥራዎች እና የሰው ኀይል ግንባታ በከፍተኛ ሁኔታ የዘመነ መኾኑን ገልጸው ነበር። ሠራዊቱ የመዋጋት እና
የቴክኖሎጂ አቅሙን በየጊዜው በማሳደግ አስተማማኝ የሀገር ጋሻ ኾኗል ማለታቸውም ይታወሳል። የትኛውንም የጠላት ሙከራ ሙሉ በሙሉ የማክሸፍ ዝግጁነቱ አስተማማኝ ደረጃ ላይ ደርሷል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
