
ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የባሕር በር ባለቤት የነበረች ብትኾንም የተለያዩ ፍላጎት ባላቸው ኃይሎች አማካኝነት በተሠራው ሴራ የባሕር በር ባለቤትነቷን እንድታጣ ተደርጓል። አሁን ላይ ግን ወደ ቀደመ የባሕር በር ባለቤትነቷ ለመመለስ ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረገች ትገኛለች።
የፖለቲካ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ቀድሞም ቢኾን ለበርካታ ዓመታት የባሕር በር ባለቤት እንደነበረች ያስረዳሉ። ዓባይ እና ቀይ ባሕር ተፈጥሮ የለገሰን ሀብቶቻችን ናቸው ያሉት ፕሮፌሰር ብሩክ ትልቅ ሕዝብ ላላት ኢትዮጵያ የባሕር በር የግድ መኾኑን ያስረዳሉ።
ከጥንት ጀምሮ እስከ ሮም እና ግሪክ ድረስ ስትገበያይበት የኖረች ብሎም ጠንካራ የንግድ እንቅስቃሴ እንደነበራት ጠቁመዋል። እስከ የመን እና ሕንድ ድረስ ትስስር የነበራት እና በንግዱ የታወቀች እንደነበረችም ተናግረዋል። ለዚህም የቀይ ባሕርን ስትጠቀምበት እንደነበር ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት የአሁን ፍላጎት እና ጥያቄ ሳይኾን የጥንት ባለቤትነት ጉዳይ እና የቀደመ ሀቋ መኾኑን ያብራራሉ። በዚህ ዘመን ሕዝቡ እና መንግሥት በአንድነት “ወደ ቀይ ባሕር እንመለስ ስንል ወደ ቀደመ ቤታችን እንመለስ ማለታችን ነው” ብለዋል። ለዚህ ፍትሐዊነቱም በታሪክ ማስረጃዎች የተደገፈ መኾኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የጂኦግራፊ እስረኛ ኾና መቀጠል እንደማትችልም ጠቁመዋል። ሀገሪቱ የታላቁ የሕዳሴ ግድብን በዓባይ ወንዝ ላይ እንዳሳካች ሁሉ የባሕር በር ባለቤትነቷንም በማስረጃ በተደገፈ ሰፊ የዲፕሎማሲ ቆራጥነት ለማሳካት ጥረት እያደረገች መኾኑንም ጠቁመዋል።
ጥያቄዎቿን በተለያዩ የዓለም መድረኮች እስከ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድረስ በማቅረብ የዲፕሎማሲ ጥረቷን ቀጥላለች ብለዋል። ዲፕሎማቶች “መለዮ አልባ ወታደሮች” ናቸው የሚሉት ፕሮፌሰሩ ሁሉም ዲፕሎማቶቿ ፍትሐዊነቷን ለዓለም ማስረዳት እንደሚጠበቅባቸው
ይመክራሉ።በርካታ የዓለም ሀገራት የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ተገቢነት እየተቀበሉት ስለመኾኑም አንስተዋል። ምሁራን እና ዲፕሎማቶችም በያሉበት ለብሔራዊ ጥቅሞቿ በአንድ ሊቆሙ እንደሚገባም አስገንዝበዋል
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
