
ከፍተኛ የሰብል አምራች ቀጣና የኾነው የምዕራብ ጎጃም ዞን በዚህ ዓመት የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሠራ ነው። በዞኑ የምርት ብክነትን ለመቀነስ በዘንድሮው የመኸር ምርት ቀድመው የደረሱ ሰብሎችን አርሶአደሮች አየሠበሠቡ ነው። በዞኑ ጃቢጠህናን ወረዳ ማንኩሳ አብደጎማ
ቀበሌ የደረሰ የጤፍ ሰብላቸውን ሲሠበሥቡ አሚኮ ያገኛቸው አርሶ አደሮች በዚህ ዓመት የተሻለ የምርት ቁመና በመኖሩ ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል። በአካባቢያቸው በቆሎ፣ ዳጉሳ እና በጤፍ መሬታቸውን በመሸፈን ቀድሞ የደረሰውን የጤፍ ሰብል በጋራ በመኾን እየሠበሠቡ
መኾናቸውንም ነው የጠቆሙት። ቀጣይ ሌሎች ሰብሎች ሲደርሱ ደግሞ ቴክኖሎችን በመጠቀም በፍጥነት ለመሠብሠብ እየሠሩ እንደሚገኙም አስረድተዋል። የጃቢ ጠህናን ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለው ሞሴ በምርት ከተሸፈነው 52 ሺህ ሔክታር መሬት ከ2 ነጥብ 5
ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነው ብለዋል። በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች የተሻለ የምርት ቁመና መኖሩን የገለጹት ኀላፊው ቀድመው የሚደርሱ የሰብል ዓይነቶችን አርሶአደሮች ሜካናይዜሽንን እና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም በፍጥነት እንዲሠበሥቡ እየተሠራ
መኾኑን ነው ያስረዱት። አሁን ላይ የበቆሎ እና የጤፍ ሰብሎች እየተሠበሠቡ ስለመኾኑ አስገንዝዋል። የምዕራብ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አጉማሴ አንተነህ በዞኑ ከ264 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች መሸፈኑን ገልጸዋል። ከዚህም
ከ14 ሚሊዮን በላይ ኩንታል እንደሚጠበቅ አንስተው አሁን ላይ ያለው የሰብል ቁመና ከሚጠበቀው በላይ ምርት ማግኘት የሚያስችል ስለመኾኑ ጠቁመዋል። በዞኑ የክላስተር አደራጃጀት መጠናከር፣ የቴክኖሎጅ አጠቃቀም ማሳደግ እና ፍትሐዊ እና ወቅታዊ የግብዓት ስርጭት
መኖር በየጊዜው ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑን ነው የገለጹት። በተለይ የምርት ብክነትን ለመቀነስ የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት ለመሠብሠብ አርሶአደሮች የደቦ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ከማድረግ ባለፈ ከ20 በላይ ኮምባይነሮች እና ከ300 በላይ የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን አማራጮች ዝግጁ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ንጉሥ ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
