
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር በሰላም፣ በአብሮነት እና በልማት ጉዳዮች ዙሪያ ከሃይማኖት አባቶች እና ከልዩ ልዩ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋር ተወያይቷል።
ውይይቱ የሃይማኖት ተቋማት የሰላም እሴቶችን በማጎልበት ዘላቂ ሰላም እና ልማት እንዲረጋገጥ የሚወጡትን ሚና ለማጠናከር ያለመ ነው።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ “ሰላም የሁሉም ሃይማኖቶች መሠረት እና የማኅበራዊ ዋስትና መረጋገጫ ነው” ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶች ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን መሠረት በማድረግ የሰላም እሴቶች እንዲጎለብቱ በማድረግ እና ለሰላም ዘብ በመቆም የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎች እንዲፋጠኑ ድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዮሐንስ አማረ መንግሥት ሰላም እና ልማትን ለማስፈን በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን ጠቁመዋል።
የሃይማኖት አባቶችም የተመዘገቡ ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሰላምን በማስፈን በኩል የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ የሃይማኖት አባቶችም ለሀገር ሰላም እና አብሮነት በጋራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት የጎንደር ቤዛዊት ማርያም ቤተክርስቲያን አገልጋይ መላከ ፀሐይ አስማረ ተድላ በፍቅር፣ በመቻቻል እና በአብሮነት ሰላምን መስበክ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት መሠረታዊ አስተምህሮ መኾኑን ጠቅሰዋል። በመመካከር እና በአንድነት ለሰላም እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ምክትል ሰብሳቢ ፓስተር አማን ሳልህ ወንጌል ሰላምን፣ አንድነትን እና ፍቅርን እንደሚሰብክ ገልጸዋል። ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን አታውቀዋል።
በጎንደር ከተማ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዩ አሕመዲን አብድቃድር ስለ ሰላም እያከናወኑ ያሉትን ሃይማኖታዊ ኀላፊነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የውይይቱ ተሳታፊዎች መንግሥት ሰላም እንዲሰፍን እያደረገ ያለውን የሰላም ጥሪ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
#አሚኮ #ሰላም_ጎንደር_ኢትዮጵያ🇪🇹
#ጎንደር #መስከረም_23_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ማህደር አድማሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
