
ግብጽ እና ኤርትራ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ እና በቀይ ባሕር ቀጣና ያላትን ተፈጥሮአዊ የጂኦፖለቲካዊ የበላይነት ለማዳከም ለዘመናት ሲሠሩ መቆየታቸውን ኢትዮጵያውያን ምሁራን በሰፊው ተንትነውታል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “The Horn of Africa: Conflict and Conflict Resolution” በሚለው ሥራቸው ግብጽ የዓባይን ውኃ በብቸኝነት ለመቆጣጠር በሚኖራት ፍላጎት ምክንያት ኢትዮጵያ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት እና የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲኖራት አትፈልግም ብለዋል።
የዓባይን ውኃ የበላይነት ለማስጠበቅ ስትልም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የውስጥ ግጭቶችን፣ ታጣቂ ቡድኖችን እና የጎረቤት ሀገራትን እንደ መሣሪያ በመጠቀም ሀገሪቱን በውስጥ ችግሮች እንድትጠመድ የማድረግ ስልት ስትከተል መቆየቷን ገልጸዋል።
ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ “A History of Modern Ethiopia (1855–1991)” በሚለው ጥናታቸው ሻቢያ ኢትዮጵያን ለማዳከም በ1960ዎቹ እና 1970ዎቹ ከግብጽ እና ከሌሎች የአረብ ሀገራት የገንዘብ፣ የመሣሪያ እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ስታገኝ እንደነበር ያስረዳሉ።
በተለይም ኢትዮጵያን በቀይ ባሕር ቀጣና አቅም የሌላት ሀገር አድርጎ ማስቀረት የግብጽ እና የኤርትራ ታሪካዊ አሰላለፍ ዋና ግብ ነበር።
በጂኦፖለቲካ እና በቀይ ባሕር ውጥረት ላይ ትኩረት አድርገው የጻፉት ተስፋዬ ታደሰ በበኩላቸው የግብጽ እና የኤርትራ ታሪካዊ አሰላለፍ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ደኅንነት የሚፈታተን፣ በባሕር በር አጠቃቀም እና በዓባይ ውኃ ፍሰት ላይ ያላትን ተፈጥሯዊ መብት እና የውኃ የባላይነት የሚጻረር መኾኑን በዝርዝር አስቀምጠዋል።
ይሁን እንጅ ኢትዮጵያ ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫናዎች ሳይበግራት ሉዓላዊነቷን እና ብሔራዊ ጥቅሟን እያስከበረች ትገኛለች። ነገም ለየትኛውም የጠላት ኀይል ሳትንበረከክ ሉዓላዊነቷን እና ብሔራዊ ጥቅሟን አስከብራ ትቀጥላለች ።
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
#አሚኮ #የግብጽና_የኤርትራ_ሴራ_በኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_23_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
