
የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የክልሉን የመንግሥት ምሥረታ አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
የመግለጫው ሙሉ ሃሳብ ቀጥሎ ቀርቧል:-
ሕዝብን በኃይል የተጫንን ሳይኾን በሕዝብ ይሁንታ የተመረጥን እንደራሴዎች ኾነን ቅቡልነት ያለው መንግሥት ለመመስረት የግድ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማከናወን ነበረብን።
በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት ለማምጣት ደግሞ ከጸረ ዴሞክራሲ እና ከጸረ ሕዝብ ኃይሎች ጋር መፋለም እና ለሀገር አንድነት፣ ሕልው እና ለዴሞክራሲ መስዋእትነት በመክፈል ነበረብን። ለዚህ የሚጠይቀውን ዋጋ ሁሉ በመክፈል የኢትዮጵያ እና የክልላችን ሕዝቦች ይሁንታ የሰጡት።
አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ታዛቢዎችም ተቀባይነቱን ያረጋገጡት፣ የመሰከሩት ነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫ በማካሄድ ለክልላዊ የመንግሥት ምሥረታ እውን መኾን ሁነኛ ማረጋገጫች ኾኗል።
በ2018 ዓ.ም በሀገር እና በክልል ደረጃ በተካሄድው ነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ ምክር ቤት በክልሉ ምርጫ በተከናወነባቸው 130 ምርጫ ክልሎች 273 መቀመጫዎች ብልጽግና ፓርቲ 257 መቀመጫዎችን በማግኘት አብላጫ ወንበር ይዟል። ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ 16 መቀመጫዎችን ይዘዋል።
ስለኾነም ምክር ቤቱ የሃሳብ ብዝኀነት የሚንሸራሸርበት፣ ለሕዝብ ይጠቅማል የሚባለው ሁሉ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማቅረብ ዕድል የሚሰጥ ምክር ቤት እንደሚኾን ይጠበቃል።
በዚህም መሠረት ምክር ቤቱ ከመስከረም 21 እስከ 22/2019 ዓ.ም በካሄደው ሳበተኛ ዙር አንደኛ መሠራች እና አንደኛ መደበኛ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ አካሂዷል። በቆይታውም የምክር ቤቱን መሪዎች እና የክልሉ መንግሥት ርእሰ መሥተዳድር የመሥተዳድር ምክር አባላትን በማዋቀር አዲሱ የክልሉ መንግሥት ተቋቁሞ ሥራውን ጀምሯል።
ምክር ቤቱ መንግሥት ከማቋቋምም ባሻገር በርእሰ መሥተዳደሩ የቀረበውን የክልሉን የ2019 በጀት ዓመት አጓጊ እና ተስፋ ሰጭ እቅድ ቀርቦ ውይይት አድርጎ አጽድቋል።
የመሠረትነው መንግሥት እና አዲሱ ምክር ቤትም የክልሉን ሕዝብ አንድነት የበለጠ በሚያሳድግ፣ በሚያጠናክር ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን መሰረት ያደረገ እና የክልሉን የፖለቲካ፣ የጾታ እና የብሔር ብዝኃነት ያከበረ እና ያስተናገደ ኾኖ የተቋቋመ ነበር።
ክልሉ ቀድሞውንም ቢኾን ብዝኃነትን በማክበር እና ዴሞክራሲን በማለማመድ ከማንኛውም አካባቢ በላይ የተለማመደና የዳበረ ልምድ በማስቀጠል ያለውን የግንባር ቀደምነት ሚና ዛሬም በተግባር አረጋግጧል።
እንደ ሕዝብ ውክልና ማግኘት ብቻ ሳይኾን መንግሥት እንደመሠረተ ፓርቲ ደግሞ በሥራ ልምዳቸው የተመሰከረላቸው፤ በአፈጻጸም ብቃታቸው፣ በትምህርት ዝግጅታቸው የተሻሉ እና ከሕዝባችን መሠረታዊ ፍላጎት በመነሳት የክልሉ መንግሥት ቀድሞ ያዘጋጀውን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ በብቃት መፈጸም እና ማስፈጸም የሚችሉ አሥፈፃሚ አካላት የተደራጁበት ስኬታማ ጉባኤ ኾኖ ተጠናቅቋል።
እነዚህ አሥፈፃሚዎች እና የምክር ቤቱ አባላት በቀጣይ አምስት ዓመታት የክልላችንን ሰላም ለማጽናት፥ ሕዝባችን በሙሉ አቅም ለእድገት እና ብልጽግና እንዲረባረብ ለማስቻል፣ የተያዙ የልማት፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ የመልካም አሥተዳደር እና ሌሎች ግቦችን ለማሳካት ከሕዝባቸው ጋር ታሪክ እንደሚሠሩ ከፍተኛ እምነት የተጣለባቸው ናቸው።
በመኾኑም መንግሥት ለሕዝቡ የገባነውን ቃል ለመፈጸም ታሪካዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ሲተጋ መላ የክልሉ ሕዝብ በሁለንተናዊ መንገድ ከጎኑ እንደማይለየውም እምነቱ የጸና ነው።
መንግሥት ሕዝቡን በትጋት እና በታታሪነት ለማገልገል ከመቸውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መኾኑን ያረጋግጣል!
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ
መስከረም 23/2019 ዓ.ም
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
