
የትምህርት ሚኒስቴር በባሕር ዳር ከተማ የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታን አስጀምሯል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት በትምህርት ዘርፉ የነበረው የትምህርት ሥርዓት መዛነፍ በአሁኑ ወቅት የከፋ ውጤትን አስከትሏል ብለዋል።
ዛሬ የተጀመረው አዳሪ ትምህርት ቤትም ለነገው ትውልድ መሠረት የሚጥል ስለመኾኑ አመላክተዋል። ትምህርትን ከአካዳሚክ ብቃት በተጨማሪ በእሴት እና በሥነ ምግባር ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ትምህርት የማኅበረሰብ ልማት መሠረት ነው ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ማኅበረሰቡም ለትምህርት ትኩረት መስጠት እና መደገፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን ወርቅነህ ባለፉት ዓመታት በክልሉ የትምህርት ዘርፉ ተጎድቶ ቆይቷል ብለዋል። በዚህ መነሻነት የክልሉ መንግሥት ለትምህርት ዘርፍ በሰጠው ትኩረት ተስፋ ሰጭ ውጤቶች መጥተዋል ነው ያሉት።
የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት እና የትምህርት መሠረተ ልማቶችን በማሟላት በኩል ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል። ትምህርት ሚኒስቴር በአማራ ክልል እያደረገው ላለው ድጋፍ ምስጋና እንደሚገባወም አንስተዋል። በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባሕር ዳር ከተማ ውብ፣ ጽዱ እና የኢንቨስትመንት ከተማ ብቻ ሳትኾን የትምህርት ከተማ እንደኾነችም ገልጸዋል። ይህንን ታሪክ የሚያስቀጥል አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ በመጀመሩም ለትምህርት ሚኒስቴር ምስጋና አቅርበዋል።
ዛሬ የተጀመረው አዳሪ ትምህርት ቤት ለነገው መሪዎች እና ተመራማሪዎች መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል። በከተማዋ ያሉ ሌሎች ትምህርት ቤቶችን ዘመኑን የዋጁ እና የተሻሉ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_23_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
