
ትምህርት ሚኒስቴር በባሕር ዳር ከተማ የ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታን አስጀምሯል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን የማስፋፋት እሳቤው የትምህርት ጥራትን ለማምጣት እና ፍትሐዊነትን ለማረረጋገጥ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የምትገነባው በዕውቀት ነው ያሉት ትምህርት ሚኒስትሩ ለነገው ትውልድ ዛሬ የሚማሩት ተማሪዎች ግብረ ገብነትን ተላብሰው፣ በባሕሪ ታንጸው፣ በዕውቀት በልጽገው እንዲማሩ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት እና የትምህርት ጥራትን በማሻሻል ኢትዮጵያን በትልቅነቷ የሚያስቡ ተማሪዎችን ማፍራት ላይ ትኩረት መደረጉንም አንስተዋል።
በባሕር ዳር ከተማ የተጀመረው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤትም 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን የሚጠጋ ብር በሚፈጅ ወጭ የሚገነባ ስለመኾኑም አንስተዋል። ግንባታው ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ትምህርት የአሻጋሪ እድገታችን መሠረት ነው ብለዋል። ይህም የነገው ዕድል የሚወሰንበት በመኾኑ የክልሉ መንግሥት በልዩ መንገድ ይገነዘባል ነው ያሉት።
የተጀመረው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤትም ተማሪዎቻችንን የላቀ ዕውቀት፣ የቴክኖሎጂ እና የሳይንስ ፈጠራ ባለቤት እንዲኾኑ የሚያስችል ነው ብለዋል። የችግር መፍቻ አቅም እና ክህሎትን የሚያዳብር ማዕከል ተደርጎ የሚወሰድ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
የትምህርት ሥርዓቱ ከቁጥር ወደ ጥራት መሸጋገር ይኖርበታል ነው ያሉት። የሥነ ምግባር እና የዜግነት ጉዳዮችን ባካተተ መንገድ እሴት ግንባታ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የክልሉ የወደፊት ዕድል በተፈጥሮ ሃብቱ ብቻ ሳይኾን በሰው ሀብቱ ጭምር የሚወሰን ነው ብለዋል። የነገውን ትውልድ በዕውቀት፣ በሥነ ምግባር፣ በሕግ አክባሪነት፣ ለማኅበረሰብ ጥቅም የሚቆም አድጎ መቅረጽ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
የዛሬውን ትውልድ ፍላጎት በማሟላት ለነገው ትውልድ አስቦ መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል። የነገው ትውልድ የሚገነባውም ያሉንን ሀብቶች መሠረት አድርጎ ሰው ሀብት ላይ መሥራት ሲቻል መኾኑንም ጠቁመዋል።
የክልሉ መንግሥት የክልሉን የትምህርት ሥርዓት ለማሻሻል ከሁሉም አጋር እና ባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_23_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
