
የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ግብጽ በዓባይ ውኃ ላይ ያላትን የሞራል እና የታሪክ ዝንፈት የሚያሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከአፍሪካ እጅግ ተጽዕኖ ፈጣሪ እና አከራካሪ ከኾኑት ግዙፍ ግድቦች አንዱ የኾነው የግብጹ የአስዋን ግድብ የከፋ ታሪካዊ እና ሰብዓዊ ጠባሳን ጥሎ ያለፈ ፕሮጀክት ነው።
የግድቡ ግንባታ ከ100 ሺህ በላይ የሚኾኑ ኑቢያውያንን ከቅድመ አያቶቻቸው መሬት ያፈናቀለ ሲኾን የማኅበረሰቡን ኅልውና እና የዕለት ከዕለት ኑሮ ክፉኛ እንዳናጋ ታሪክ ምስክር ነው።
ግብጽ ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት ስትገነባ የሌሎችን ተፋሰስ ሀገራት መብት ሙሉ በሙሉ የጣሰ የብቻ እርምጃ መውሰዷም አግባብነት እንደሌለው ኮንነዋል። በወቅቱ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የውይይት ጥሪ ብታቀርብም የግድቡ ግንባታ ያለ ኢትዮጵያ ስምምነት እና ዕውቅና ተካሂዷል።
የግብጽ አድራጎት በወቅቱ ዓለም አቀፍ ስጋትን የፈጠረ እንደነበር ከ1952 እስከ 1960 ባለው ጊዜ ውስጥ የተመዘገቡ 15 ይፋዊ የአሜሪካ እና የእንግሊዝ መዛግብት ያስረዳሉ። እነዚህ ሰነዶች በሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ተሳትፎ እና ውይይት አለመኖሩን የተመለከቱ አለመግባባቶችን በግልጽ አስፍረዋል።
በ1950ዎቹ ኢትዮጵያ ራሷ በአስዋን ግድብ እና ከዚያ ቀደም በነበሩ የዓባይ ውኃ ስምምነቶች ዙሪያ ምክክር ባለመደረጉ በይፋ የተቃወመችበት ታሪክ መኖሩን አስታውሰዋል። ዛሬ ላይ ግብጽ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት አላማከረችም በሚል ምክንያት ብቻ ኢትዮጵያን ለመተቸት ምንም ዓይነት የሞራል መሠረት የላትም።
ግብጽ የሕዳሴውን ግድብ አስመልክቶ ኢትዮጵያን ከመተቸቷ በፊት አስዋን ግድብን ያለ ኢትዮጵያ ስምምነት ለምን እንደገነባች እና የ100 ሺህ ኑቢያውያንን ሕይወት ለምን እንዳመሰቃቀለች ለታሪክ እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማብራራት ይጠበቅባታል።
ከግብጽ የብቻ የታሪክ እርምጃ በተቃራኒው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዘመናዊ የሕግ ማዕቀፍን የተከተለ እና ለቀጣናዊ ትብብር ቅድሚያ የሰጠ ነው።
የሕዳሴው ግድብ በግብጽ፣ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል በተፈረመው የ2015ቱ የመርኾዎች ስምምነት (DoP) በኩል ሕጋዊ ምላሽ ያገኘ እና በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ መኾኑ የኢትዮጵያን ትክክለኛ የሞራል እና የሕግ የበላይነት ያረጋግጣል።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ 🇪🇹
#አሚኮ #ሰላም #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_23_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
