
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ አካሂዷል።
በበጀት ዓመቱ ውጤታማ የሰላም ማስከበር ሥራ በማከናወኗ ከተማዋ በክልሉ አንደኛ ደረጃን ይዛ አጠናቅቃለች።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የከተማዋን የኢንቨስትመንት እና የልማት ተወዳዳሪነት ለማስቀጠል ይሠራል ብለዋል። ደብረ ብርሃን በልማት ግንባር ቀደም ልትኾን የቻለችው ማኅበረሰቡ ለሰላም በሚሰጠው ከፍተኛ ቦታ መኾኑን አብራርተዋል።
በበጀት ዓመቱ በጸጥታ ኃይሎች መካከል የነበረው ከፍተኛ የመናበብ እና የቅንጅት ባሕል የሚመሰገን እንደነበርም ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ የራሱን እና የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ረገድ የሰላሙ ዘብ እና ባለቤት እንዲኾንም ጥሪ አቅርበዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ዳንኤል እሸቴ የከተማዋን ሰላም እና ልማት ለማስተጓጎል የተደረጉ ጥረቶችን ማክሸፍ ተችሏል ብለዋል። ይህም ደብረ ብርሃን የሰላም አምባሳደርነቷን ጠብቃ የጀመረችውን ፈጣን የኢንቨስትመንት ጉዞ እንድትቀጥል አድርጓታል ነው ያሉት።
በ2019 የበጀት ዓመትም የታየውን አንድነት ስንቅ በማድረግ የተገኘውን ደረጃ ማስጠበቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሥራ ኀላፊ የኾኑት ሜጄር ጄኔራል ነገሬ ቶሌራ የጸጥታ አካላት እና የሕዝቡ ቅንጅት ለሀገሪቱ ሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
የውስጥ እና የውጭ ጥፋት ኃይሎች ሀገሪቱን ለማፍረስ ያቀዱትን ሴራ ማክሸፍ መቻሉንም አብራርተዋል።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ 🇪🇹
#አሚኮ #ሰላም #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ደብረ_ብርሃን #መስከረም_23_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ደጀኔ በቀለ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
