‎የካይሮ ራስ ምታት ፦ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና የሕዳሴው ትውልድ 🇪🇹

14

‎የኢትዮጵያ እና የግብጽ ግንኙነት የጂኦ-ፖለቲካ ትንቅንቅ የሚታይበት ነው። ካይሮ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት በመኾን በገሃድ ትታወቃለች። የጠላትነቷ መነሻም ከኢትዮጵያ አብራክ የሚፈልቀውን የዓባይ ወንዝ ለዘመናት በብቻኝነት የመጠቀም መሻቷ ነው።
‎
‎ይህን መሻቷን ለማስቀጠልም በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረሙ እና ኢትዮጵያን ያገለሉ ፍጹም ኢ-ፍትሐዊ ስምምነቶችን እንደ ሽፋን በመጠቀም ኢትዮጵያ ዓባይን እንዳትገድብ ስትሠራ መኖሯ ታሪካዊ ጠላትነቷን ያገዝፈዋል።
‎
‎ሰላም እና መረጋጋት ያላት ኢትዮጵያ ለብቻ የመጠቀም ፍላጎቴ ትልቅ ስጋት ናት ብላ የፈረጀችው ግብጽ ከድሮ ጀምራ እንደ ኤርትራ ያሉ የጎረቤት ኀይሎችን በመጠቀም እና የውስጥ ባንዳዎችን በመደገፍ የኢትዮጵያን ሰላም ለማናጋት ስትሠራ ኖራለች። በሌላ በኩል የዓለምን ማኅበረሰብ ለማሳሳት እና የኢትዮጵያን መልካም ስም ለማጉደፍ ተደጋጋሚ የሀሰት ውንጀላዎችን አቅርባለች።
‎
‎የካይሮ ዋነኛ ስትራቴጂካዊ ዓላማ ግልጽ ነው፤ ኢትዮጵያን በውስጥ ግጭት በመጥመድ የተፈጥሮ ሃብቷን እንዳታለማ እና በድህነት እንድትኖር ማድረግ ነበር።
‎
‎ኢትዮጵያ ይህንን ሁሉ የግብጽ የዘመናት ሴራ በጠንካራ ዲፕሎማሲ በማክሸፍ እና የተደቀኑ የውክልና ጦርነቶችን በብልሃት በማለፍ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቃለች።
‎
‎ይህም የግብጽ የዘመናት የውኃ ፖለቲካ የበላይነት ያከተመበት እና በዲፕሎማሲው መድረክ ትልቅ ሽንፈት የተጎነጨችበት ታሪካዊ ክስተት ኾኖ ተመዝግቧል። በአንጻሩ ግድቡ የኢትዮጵያውያን የአንድነት፣ የጥንካሬ እና የሉዓላዊነት ሕያው ምስክር መኾን ችሏል።
‎
‎የታሪክ አቅጣጫ የቀየረው ይህ ግዙፍ ግድብ ተጠናቅቆ ሲመረቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ባደረጉት ንግግር “ሕዳሴ የትናንት ቁጭት ማሠሪያ፤ የነገ ንጋት ማብሠሪያ ነው። ግድቡ የኢትዮጵያን ጥልቅ ጨለማ፣ ጥልቅ እንቅልፍ ያነቃ ነው” ማለታቸውን እናስታውሳለን።
‎
‎”እኛ ኢትዮጵያውያን የማይሞት ስም እንጅ የማይሞት አካል የለንም። አካላችን ሞቶ የማይሞት ስም እና አሻራ ለማኖር የምንተጋ ሕዝቦች ስለኾንን ከእኛ ጋር መጋጨት ሳይኾን መስማማት ብቻ ነው የሚያዋጣው” በማለት ኢትዮጵያ ዕድገቷን እንዳታረጋግጥ ለሚሠሩ አካላት ጥብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።
‎
‎ምክንያቱን ሲያብራሩም በሺህ ዘመናት የሞከሩን አንዴም እንዳልተሳካላቸው፣ እኛ ግን በሺህ ዘመናት ያላሳካነውን ግድብ አጠናቀናል በማለት ኢትዮጵያ ሁሌም አሸናፊ መኾኗን አብስረዋል።
‎
‎ይሁንና የሕዳሴው ግድብ እውን መኾን ግብጽን አሁንም እያንገበገባት ይገኛል። ለዚህ ማሳያው ደግሞ አሁንም የውስጥ ባንዳዎችን በመደገፍ እና ግልጽ የውክልና ጦርነት በመክፈት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመገዳደር እያደረገች የምትገኘው ጥረት የዚሁ የጥፋት ተልዕኮዋ እና የጥንተ ጠላትነቷ አካል ነው።
‎
‎ኾኖም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ትውልድ ዛሬም የተደቀነውን አዲስ ሴራ በጋራ ክንዱ በድል ለመወጣት ዝግጁ በመኾኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ጠላቶች መቼም አይሳካላቸውም።
‎
‎#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
‎
‎#AMECO #GERD #ETHIOPIA🇪🇹​
‎
‎#ባሕር_ዳር #መስከረም_23_2019_ዓ_ም
‎
‎በአድኖ ማርቆስ
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🇪🇹 የግብጽ እና ኤርትራ የዓባይን ጸጋ እና የቀይ ባሕርን ራዕይ የማደናቀፍ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሴራ
Next articleከተበላሸው የትላንት ታሪካዊ አካሄዱ ሳይታረም ዛሬም የሴራ ፖለቲካውን የሚጎነጉነው ሻቢያ