🇪🇹 የግብጽ እና ኤርትራ የዓባይን ጸጋ እና የቀይ ባሕርን ራዕይ የማደናቀፍ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሴራ

25

 

ኢትዮጵያ ከዓባይ ውኃ፣ ከቀይ ባሕር ጂኦ-ፖለቲካ፣ ከታሪካዊ የድል አድራጊነት ማማዋ እና ከኢኮኖሚ ዕድገቷ ጋር በተያያዘ የውጭ ኅይሎች የውስጥ ክፍተቷን በመጠቀም ሀገሪቱን ለማዳከም ያልተቋረጠ ጥረት ያደርጋሉ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) “የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ቀጥታ ጦርነት ከማድረግ ይልቅ በውስጣችን ያሉ የሥልጣን ጥመኞችን እና ባንዳዎችን በገንዘብ እና በመሣሪያ በመደገፍ እርስ በእርስ እንድንጠፋፋ ያደርጋሉ።” ይህም የውስጥ አንድነት መላላት ለውጭ ጠላት መግቢያ ቀዳዳ ኾኗል ሲሉ በአንድ ወቅት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጸው ነበር።

ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይዛ የባሕር በር አልባ ኾና መቀጠል እንደማትችል እና ቀይ ባሕር የሕልውና ጉዳይ መኾኑንም አብራርተዋል። ይሁን እንጂ የውጭ ኀይሎች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እና የጂኦ-ፖለቲካ ተጽዕኖ መስፋፋት በስጋት እየተመለከቱት ስለመኾኑም ነው የገለጹት።

ከውኃ ፖለቲካ አኳያ የውጭ ኅይሎች ኢትዮጵያን በውስጥ ግጭት ጠምደው ለማስቀረት የሚያደርጉት ሴራ በቀላል የሚታይ አይደለም ባይ ናቸው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና የውኃ ፖለቲካ ምሁሩ ፕሮፌሰር ያቆብ አርሳኖ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት (በተለይም ግብጽ) በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረሙ ኢ-ፍትሐዊ ስምምነቶችን መነሻ በማድረግ በዓባይ ውኃ ላይ ያላቸውን የብቻ ተጠቃሚነት ለማስቀጠል እንደሚፈልጉ ይናገራሉ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ይህንን የዘመናት ብዝበዛ ሰብሮታል። ግብጽ በቀጥታ ጦርነት ውስጥ ከመግባት ይልቅ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ አማጺያንን በማስታጠቅ፣ የዲፕሎማሲ ዘመቻ በማካሄድ እና የውስጥ አለመረጋጋት በመፍጠር የልማት ሥራዎች እንዳይሳኩ ስትሠራ ቆይታለች፤ አሁንም ቀጥላለች ይላሉ።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ የድል አድራጊነት እና የነጻነት ተምሳሌትነት ሌላው የውጭ ኅይሎች ኢትዮጵያ ላይ እንዲዘምቱ እንዳደረጋቸውም ያብራራሉ።

ብርጋዴር ጀኔራል ካሳዬ ጨመዳ በአንድ ወቅት ግብጽ ኢትዮጵያን 15 ጊዜ የወረረች መኾኑን በማስታወስ ኹሉም ግን በኢትዮጵያ አሸናፊነት መጠናቀቁን ጠቁመዋል።

ዓድዋ ላይ የተመዘገበው ድል የምዕራባውያንን የነጭ የበላይነት ትርክት የሰበረ በመኾኑ ኢትዮጵያ ሁሌም በዓለም አቀፍ ኀይሎች በጥርጣሬ እንድትታይ አድርጓታልም ይላሉ።

ካናዳዊቷ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና የጸጥታ ጉዳዮች ምሁር ፕሮፌሰር አን ፊትዝጀራልድ ምዕራባውያን ኅይሎች በአፍሪካ ቀንድ ያላቸውን የጂኦ-ፖለቲካ ፍላጎት ለማስፈጸም ሲሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭቶች በእጅ አዙር እያደረጉ መኾኑንም መስክረዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ፈተናዎች ምንጫቸው ታሪካዊ፣ ጂኦ-ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቢኾንም የሴራው ዋነኛ ማስፈጸሚያ ግን የራሷ የውስጥ ክፍፍል እና ኀላፊነት የማይሰማቸው የውስጥ ኅይሎች ናቸው ባይ ናቸው።

ታሪካዊውን የህልውና ፈተና ለመቀልበስ ብቸኛው መንገድ በማንኛውም የፖለቲካ ልዩነት ውስጥ ለሀገር ሉዓላዊነት እና ሀገራዊ ጥቅም ቀይ መስመር የሚያሰምር ጠንካራ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ስለመኾኑም ይጠቁማሉ።

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!

#Ameco #Sovereignty​ #EthiopianPride🇪🇹​

#ባሕር_ዳር #መስከረም_23_2019_ዓ_ም

በስማቸው አጥናፍ

‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየኢሬቻ በዓል እየተከበረ ነው።
Next article‎የካይሮ ራስ ምታት ፦ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና የሕዳሴው ትውልድ 🇪🇹