
🌴
”ውብ ሀገሬ፣
ውብ ሀገሬ፣
በአንቺ እኮ ነው መከበሬ”
የሚለው ዜማ ተራ እንጉርጉሮ አይደለም። የዘመናት ቁጭት፣ የሀገር ፍቅር እና የነጻነት ወኔ መግለጫ እንጂ።
መስከረም 19/2019 ዓ.ም በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተካሄደው የኢትዮጵያ እና ሴኔጋል ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ይህ ዜማ በሺዎች በሚቆጠሩ የስፖርት አፍቃሪዎች ኅብረ ድምጽ ሲስተጋባ የስታዲየሙን ምድር ያናወጠ የብዙዎችን ሆድ ያስባሰ ልዩ ክስተት ነበር።
ፀሐይ በጣና ላይ ጉልበቷን ሳታሳይ ጀምሮ የባሕር ዳር ጎዳናዎች በስፖርት አፍቃሪያን ተሞልተው ነበር። ቤት የቀረ ሰው የሌለ እስኪመስል ድረስ። ደጋፊዎች በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ ዓላማዎች አምረው ከልብ የመነጨ የሀገር ፍቅርን በተግባር አንጸባርቀዋል። የከተማዋ ነዋሪ እንግዳ ተቀባይነቱን የኳስ አፍቃሪው ደግሞ ለዓመታት የራቀው የሜዳ ላይ ድጋፍ የታደሰውን ጥማቱን በስፖርታዊ ጨዋነት እና በፍቅር ገልጾበታል።
ረጅም ሰልፍ፣ የሚያቃጥል ፀሐይ እና ድካም ወንድሞቻቸውን በአካል አግኝተው ከጎናችሁ ነን ለማለት የተሰለፉትን ደጋፊዎች ፍቅር አላስቆመውም። ደጋፊው በጋለ ስሜት እና እልልታ ለቡድኑ ሁለተኛ ሳንባ ኾኖ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ድምጹን ሳይነፍግ ደግፏል። አጀግኗል፣ ወኔም ኾኗል።
ውጤቱ ምንም ይሁን ምን የባሕር ዳር እና አካባቢው ሕዝብ ያስመሰከረው ስፖርታዊ ጨዋነት፣ ሀገር ወዳድነት እና ደመቅ ያለ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕል የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በጨዋታው ዋዜማ መግለጫ ሲሰጡ ያመላከቱትን እና የተማመኑበትን እውነት በተግባር አረጋግጧል።
ባሕር ዳር አሁንም ትልልቅ አሕጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በብቃት የማስተናገድ አቅሟን፣ ውበቷን እና ጨዋነቷን ለመላው ዓለም በድጋሚ አሳይታለች። የጣናዋ እመቤት የፍቅር እና የወኔ ድግሷን በውጤታማነት ማጠናቀቋንም የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ገልጸዋል።
💬 እርስዎስ ባሕር ዳር ባስተናገደችው የኢትዮጵያ እና የሴኔጋል ጨዋታ ላይ ምን ሀሳብ አላችሁ?
በኮሜንት መስጫ ላይ አጋሩን?👇
#አሚኮ #ስፖርት #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_23_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
