
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከከተማዋ የመንግሥት ሠራተኞች ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በውይይቱ የተሳተፉት የመንግሥት ሠራተኞች ተገልጋዮች ወደ ተቋማት በሚመጡበት ወቅት የመልካም አሥተዳደር እጦት እንዳይገጥማቸው ሕዝብን በተገቢው መንገድ ለማገልገል ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ነፃነት መንግሥቴ የዜጎችን እንግልት ለመቀነስ እና የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን ለማዘመን የዲጂታል አሠራርን የመተግበር ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ መኮንን በበኩላቸው የመንግሥት ሠራተኞች ሕዝብን እና መንግሥትን የሚያቀራርቡ ሥራዎችን በመሥራት የልማት እና የሰላም ማስከበር ሂደቱን ሊያፋጥኑ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ እንደተናገሩት የመንግሥት ሠራተኛው ብሔራዊ ጥቅምን በማስጠበቅ፣ የሰላም እና የልማት ሂደቱን በመደገፍ እንዲሁም በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የመልካም አሥተዳደር ዘርፎች የተሰጡትን ኀላፊነቶች በብቃት እና በቁርጠኝነት መወጣት አለበት።
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዮሐንስ አማረ የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ዳር ለማድረስ እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ሠራተኛው የተጣለበትን ኀላፊነት በታማኝነት መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
