የባሕር በር – የዛሬው ትውልድ የነገ ዓድዋ!

4
ኢትዮጵያ የጂኦፖለቲካዊ አቀማመጧን በመጠቀም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላም፣ በንግድ እና በጋራ ልማት የመተሳሰር ራዕይን አንገብጋቢ ብሔራዊ ጉዳይ አድርጋለች። የባሕር በር ጥያቄ የዛሬው ትውልድ የትኩረት ማዕከል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ሌሎችን የመጉዳት ወይም የጦርነት ዓላማ የሌለው መኾኑን ግልጽ አድርገዋል። ይልቁንም የባሕር በር ፈጣን ዕድገት ላለው እና እያደገ ለሚገኘው ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ ቀጣይነት ወሳኝ የሕልውና ጉዳይ እንጂ።
ከሀገሪቱ የሕዝብ ብዛት፣ ከጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እና ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አንጻር የባሕር በር ማግኘት ማንም ሊክደው የማይችል ፍትሐዊ ጥያቄ ሲኾን የዛሬው ትውልድ ሀገራዊ እና ታሪካዊ ኀላፊነቱን የሚወጣበት ትውልዳዊ አደራም ነው። ኢትዮጵያ በባሕር በር ላይ ያላት ጥገኝነት
ኢኮኖሚዋን ከመፈተኑም በላይ ለደኅንነቷም ኾነ ለንግድ እንቅስቃሴዋ እንቅፋት ነው። የዛሬው ትውልድ የሚለካው በጦርነት እና በግጭት ሳይኾን በንግግር፣ በዲፕሎማሲ እና በጋራ ልማት ማሸነፍ ሲችል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ሃሳብ ሲያስረዱ “እኛ የምንፈልገው በንግግር፣
በውይይት እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ነው። ከማንም ጋር ጦርነት ውስጥ ለመግባት ሃሳብ የለንም” በማለት አጠናክረውታል። ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት የሌሎችን ሉዓላዊነት የሚጻረር ሳይኾን፣ በንግድ ልውውጥ፣ በወደብ
መጋራት እና በኢኮኖሚ ትስስር ላይ የተመሠረተ ሰላማዊ አካሄድ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የዓድዋ አባቶች ሀገራቸውን ከቅኝ ግዛት እንዳስጠበቁ ሁሉ የዛሬው ትውልድም የኢኮኖሚ ነጻነቱን የሚያረጋግጥበት እና የባሕር በር ባለቤት የሚኾንበትን ታሪክ በደማቁ ይጽፋል። ይህን ትውልድ ታሪክ የሚያመሠግነው በሰጠው ምላሽ መኾኑን አስቦ በጋራ መሰለፍ ይገባል።
የባሕር በር ጥያቄ የዛሬው ትውልድ ትልቁ ፈተና እና የትግል አውድ ነው። ጥያቄው የፍትሕ፣ የዕድገት እና የህልውና ጉዳይ በመኾኑ ትውልዱ በዲፕሎማሲ፣ በትዕግስት እና በብልሀት አሸንፎ የወደፊቱን የኢትዮጵያ ታሪክ በደማቅ ቀለም የሚመዘግብበት ሌላኛው ዓድዋ ኾኖ ወደፊት ይጠቀሳል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሰላም፣ የቱሪዝም እና የኮንፈረንስ ማዕከልነቷን ያረጋገጠችው ባሕር ዳር