
ባሕር ዳር ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን፣ ስፖርታዊ ሁነቶችን እና መጠነ ሰፊ ኮንፈረንሶችን በስኬት ማስተናገዷ በከተማዋ አስተማማኝ ሰላም እና መረጋጋት መኖሩን ለሀገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያሳየችበት ሕያው ምስክር ነው።
እነዚህ ትላልቅ ሁነቶች በሰላማዊ መንገድ መከናወናቸው የከተማዋን ገጽታ ከመገንባት ባለፈ ለከተማዋ ሁለንተናዊ እድገት ያለው አስተዋጽኦም ከፍተኛ ነው። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባሕር ዳር ትላልቅ ሁነቶችን ማስተናገድ መቻሏ የከተማዋን አስተማማኝ ጸጥታ በተግባር የሚያረጋግጥ መኾኑን መናገራቸው ይታወሳል።
በሺዎች የሚቆጠሩ እንግዶች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ስፖርተኞች እና ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ወደ ከተማዋ በነጻነት መጥተው መሳተፋቸው ከተማዋ ሰላሟ የሰፈነ እና ለእንግዶቿ ምቹ መኾኗን ማስመስከሩን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የባሕር ዳር እና የአካባቢው ነዋሪ በመልካም የእንግዳ ተቀባይነት እሴት እንግዶችን ማስተናገዳቸው የከተማዋ ነዋሪ ለሰላም እና ለልማት ያለውን ጽኑ ፍላጎት የሚያንጸባርቅ መኾኑን ጠቅሰዋል።
በባሕር ዳር ከተማ ከተከናወኑ ሁነቶች ጋር ተያይዞ የወጡ የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም ሁነቶቹ በከተማዋ ለሚገኙ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የጎብኝ መዳረሻዎች ለባሕል አልባሳት እና የእጅ ጥበብ አቅራቢዎች የገቢ መነቃቃት ፈጥረዋል።
እንዲህ ዓይነት ሁነቶች ለከተማዋ የሚያስገኟቸው ዘለቄታዊ ጥቅሞች ይኖራሉ። አንደኛው የኢንቨስትመንት እና የመሠረተ ልማት እድገት መፍጠር ነው። እንደ ባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም፣ በኮሪደር ልማት እየተሠሩ እንዳሉ መሠረተ ልማቶች እና ሌሎችም ሥራዎች ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሠሩ እና ሥራዎች እንዲቀጥሉ ከማድረጉም በላይ ሰላም እና ምቹ ሁኔታን የተመለከቱ ባለሀብቶች በክልሉ መዋዕለ ንዋይ እንዲያፈስሱ መንገድ ይከፍታሉ።
ማኅበራዊ ትስስር እና ብሔራዊ አንድነትንም ይፈጥራሉ፤ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ እንግዶች እና ስፖርተኞች በባሕል እና በእሴት ልውውጥ ብሔራዊ አንድነትን ያጠናክራሉ። እንዲህ አይነት ሁነቶች እና ኮንፈረንሶች የሥነ ልቦና መነቃቃትንም ይፈጥራሉ። የከተማዋ ወጣቶች እና ነዋሪዎች በከተማቸው የመኩራት እና የሥነ ልቦና መነቃቃት ስሜት እንዲኖራቸውም ያደርጋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
