ተማሪዎች ከክፍል ክፍል የሚዘዋወሩት በብቃት ብቻ ነው።

4
ነገ ሀገርን የሚረከቡ ብቁ ዜጎችን ለማፍራት ትምህርት ቤቶችን ከማሻሻል ባለፈ፣ በመማር ማስተማር ሂደት ብቃትን ማረጋገጥ እንደ ሀገር በትኩረት እየተሠራ ይገኛል። በአማራ ክልልም ባለፉት ዓመታት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።
በአማራ ክልል​ ትምህርትት ቢሮ ምክትል ኀላፊ እየሩስ መንግሥቱ እንደገለጹት በሥርዓተ ትምህርቱ የተቀመጡ እሳቤዎችን ወደ ተግባር በመለወጥ እየተሠራ ይገኛል። የምዘና ሥርዓቱ እና የመማር ማስተማር ሥራውም ብቃትን መሠረት ያደረገ እንዲኾን መደረጉን አንስተዋል።
ባለፉት ዓመታት ሲተገበር የቆየው የመማር ማስተማር ተግባር ተኮር እና ብቃትን መሠረት ያደረገ መኾኑንም ነው የገለጹት። በተለይም ተማሪዎች ከክፍል ወደ ክፍል የሚዘዋወሩትጊዜ ቆጥረው ሳይኾን፣ የሚጠበቅባቸውን ዕውቀት እና ክህሎት አግኝተው እንዲኾን እየተደረገ ነው።
በዚህም ተማሪዎች ምን ያህል ዕውቀት እና ክህሎት እንዳገኙ እየተመዘነ እና እየተረጋገጠ ወደ ቀጣዩ ክፍል እንዲሸጋገሩ ይደረጋሉ ነው ያሉት።
​የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የመምህራን ልማት እና የትምህርት አመራር ብቃትን ማሳደግ ሌላው ተግባር እንደኾነም ነው ያስረዱት። መምህራን ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ማስተካከያ የክረምት ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ በዕቅድ መሠራቱንም ገልጸዋል።
በ2018በጀት ዓመት በክረምት ከ10 ሺህ በላይ መምህራን ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓልም ብለዋል። በትምህርት ቤት ውስጥም ተከታታይ የሙያ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ በማድረግ፣ እርስ በእርስ ልምድ በመለዋወጥ እና ተመሳሳይ የትምህርት ይዘት የሚያስተምሩ መምህራን ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መሠራቱንም ገልጸዋል።
ይህም የተማሪዎችን ችሎታ ለማሳደግ ትልቅ አቅም ነው። በዚህም የመምህራንን እና የትምህርት አመራሩን አቅም የመገንባት ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
​እንደ ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ ገለጻ ታዳጊዎች ከሕፃንነታቸው መሠረት ይዘው እንዲያድጉ ለማድረግ በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መኾንም ነው ያስረዱት።
​ሁሉንም ተማሪዎች በየክፍል ደረጃቸው የሚጠበቅባቸውን ዕውቀት እና ክህሎት አስጨብጦ ወደ ቀጣዩ ክፍል ከማሸጋገር ባሻገር፣ ክልል አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ተፈታኝ ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተመላክቷል።
ዘጋቢ:- ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየአየር ንብረት ለውጥ ቀጣዩ የጤና ሥጋት?
Next articleየሰላም፣ የቱሪዝም እና የኮንፈረንስ ማዕከልነቷን ያረጋገጠችው ባሕር ዳር