
ባሕር ዳር: ጥቅምት 23/2019 ዓ.ም (አሚኮ) እየጨመረ የመጣው የሙቀት መጠን፣ ድርቅ፣ መደበኛ ያልኾነ የዝናብ ሥርጭት እና ጎርፍ የምግብ እጥረትን ይፈጥራሉ። በተጨማሪም ለተላላፊ በሽታዎች ሥርጭት መስፋፋት ምክኒያት ይኾናሉ።
ሲጂቲኤን አፍሪካ በአፍሪካ የሚገኙ በርካታ ቤተሰቦች ህይወታቸው የተመሰረተው በዝናብ እርሻ ላይ በመኾኑ በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ሰብላቸው እና እንስሳቶቻቸው ሲጠፉ ለዓመታት ያፈሩት ሃብት በአንድ ጊዜ ይወድማል። ይህም ድህነትን ያባብሳል፣ የወደፊት ተስፋቸውንም ያጨልመዋል ይላል።
በተጨማሪም የጎርፍ መከሰት የንፁህ ውሃ ምንጮችን በመበከል ለውሃ ወለድ በሽታ ዜጎችን ይዳርጋል። ድርቅ ደግሞ የንጹህ ውኃ እጥረት በመፍጠር እና የንጽህና አጠባበቅ ኹኔታ ላይ ችግር በመፍጠር ለበሽታ ይጋልጣል።
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ግምት እንደሚያሳየው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከምግብ እጥረት፣ ከወባ፣ ከተቅማጥ እና ከከፍተኛ ሙቀት ጋር ተያይዞ በየዓመቱ ተጨማሪ 250 ሺህ ሰዎች ህይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ።
ሴቶች፣ ህፃናት፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች እና ተፈናቃዮች የዚህ ቀውስ ዋና ሰለባዎች ናቸው። የኑሮ ውድቀት እና የምጣኔ ሃብት መዳከም ሴቶችን ለአስገዳጅ የሰውነት ንግድ፣ ለጥቃት እና ለተለያዩ የጤና አደጋዎች ያጋልጣቸዋል።
በተጨማሪም ድርቅ ሴቶችና ሴት ልጆች ውኃ ፍለጋ ረጅም መንገድ እንዲጓዙ በማድረግ ለተለያዩ ጥቃቶች ያጋልጣቸዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ከሚያደርጉ ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ነው። ይሄም ዜጎች ለተለያዩ የጤና እክሎች እንዲጋለጡ አንዱ ምክኒያት ይኾናል።
ችግሩን ለመቋቋም ትክክለኛ መረጃን መሠረት ያደረገ አሠራር መከተልን እና ለጤና ዘርፍ የሚኾን የአየር ንብረት ለውጥ ማስታገሻ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት ወሳኝ መኾኑን ምንጩ አንስቷል።
ሀገራት የሕዝብ ቁጥር፣ የጤና እና የአየር ንብረት መረጃዎችን ያቀናጀ አሠራር ዘርግተው አስቀድመው ዝግጅት ማድረግ እንደሚኖርባቸው ዘገባው አሳስቧል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይኹኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
