
የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብት ሰፊ አማራጮችን እና ጸጋዎችን ያካተተ ነው። ከራስ ደጀን እስከ ዳሎል የሚዘልቀው ውብ መልከዓ ምድር፣ የሕዝቦቿ ብዝኃ ባሕል፣ ታሪክ፣ እና አያሌ ቅርሶች የሀገሪቱን የብዝኀ ቱሪዝም ጸጋን በግልጽ ያሳያል።
አሁናዊ የከተሞች የኮሪደር ልማትም ሌላው የቱሪዝም ጸጋ እና የመስህብ ሃብት ኾኗል። ገጽታን በመገንባት ጎብኝዎችን ለመሳብ አስተዋጽኦ እያበረከተም ይገኛል። አዲስ አበባን ጨምሮ በክልሎች ዘመናዊ የመሠብሠቢያ እና የመስተንግዶ ተቋማት መሥፋፋትም ለኮንፈረንስ ቱሪዝም እድገት አዲስ በር እየከፈተ ነው።
በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር እና በገበታ ለትውልድ መርሐ ግብሮች የተገነቡት ታላላቅ ፕሮጄክቶችም ለቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ አቅም ፈጥሮላታል። ከ6 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የዕፅዋት ዝርያዎች፣ እንደ ዋሊያ አይቤክስ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ እና ቀይ ቀበሮ ያሉ ብርቅየ እንስሳት ባለቤት መኾኗም ለአድቬንቸር ቱሪዝም ተመራጭ ያደርጋታል።
እነዚህ ተፈጥሯዊ እና ባሕላዊ ጸጋዎች ተደምረው ኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ የቱሪስት መዳረሻ እና የቱሪዝም ባለጸጋ እንድትኾን አስችሏታል። በዚህም ሀገሪቱን ተወዳዳሪ እና አስተማማኝ የቱሪስት መዳረሻ የማድረግ ርዕይ ሰንቃ ጸጋዎቿን ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር የሚያስችሉ የፖሊሲ ማሻሻያ አድርጋለች።
ባለፉት ዓመታት ባከናወነቻቸው አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶች፣ የቅርስ ጥገና እና በሚስተዋወቁ ሥራዎች ተስፋ ሰጭ ውጤቶችን አስመዝግባለች።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2018 በጀት ዓመት ብቻ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የዓለም አቀፍ ጎብኝዎች ሀገሪቱን ጎብኝተዋታል። ከዚህም 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።
በተመሳሳይ ከ50 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ ያሉ ቦታዎችን ጎብኝተዋል። ይህም ካለፈው ዓመት በ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ጭማሪ ያሳየ ነው። ከ79 ቢሊዮን ብር በላይም ገቢም አስገኝቷል።
በኮንፈረንስ ቱሪዝምም ኢትዮጵያ በርካታ የዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በስኬት ማስተናገድ ችላለች። ይህም ካለፉት ሁለት ዓመታት አንጻር ከፍተኛ ብልጫ ያለው ነው።
#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_23_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
