የኮዳውን ውኃ በርህራሄ የሚያካፍል – ጀግናም፣ ትሁትም ወታደር!

6

 

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሀገር ሕልውና ጋር የተሳሰረ የጀግንነት ታሪክ ባለቤት ነው። ሠራዊቱ የጦር መሣሪያን ብቻ በመያዝ የሚታወቅ ሳይኾን ከሕዝብ ማሕጸን ወጥቶ ለሕዝብ ሕይወት እና ክብር ሲል ራሱን የሚሰጥ ጽኑ ሕዝባዊ መሠረት ያለው ኃይል ነው።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ የብሔራዊ ጉዳዮች ምርምር ልማት መምሪያ ኀላፊ ሥራው ደማስ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት ከራስ በፊት ሀገርን እና ሕዝብን የሚያስቀድም ነው ብለዋል።

ሠራዊቱ በምርምር እና ትምህርት አዋቂ፣ በጤና ባለሙያነት ሕክምና ሰጪ፣ በግብርና ሥራ አብቃይ፣ ለተቸገረ ማኅበረሰብ የራሱን ሬሽን እና የኮዳ ውኃ በርህራሄ የሚያካፍል ታላቅ ሕዝባዊ ሠራዊት እንደኾነ ነው የተናገሩት።

በእርግጥም ሠራዊቱ በሰላም ጊዜ ማረሻውን በመጨበጥ የኢኮኖሚ ነጻነትን ለማረጋገጥ ከፊት ተሰልፎ ሠርቷል፤ ይሠራልም ብለዋል። ሀገር በምትፈተንበት፣ የብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ላይ በሚወድቅበት እና ሉዓላዊነት በከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ በሚገባበት ሰዓት ደግሞ እንደማይበገር ግንብ ቆሞ የዜጎች የመጨረሻ መጠለያ ይኾናል ነው ያሉት።

ሠራዊቱ ለሰላም ሲል መሬቱን፣ ተራራውን እና ጫካውን ተሻግሮ አጥንቱን ከስክሷል፤ ደሙንም አፍስሷል። ይህ መስዋዕትነት የሀገርን አንድነት ከማስጠበቁም በላይ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ሳይንስ መመዘኛዎችን በብቃት ያሟላ መኾኑን በውጊያ አውድ እና በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች አስመስክሯል።

የዘመኑ መከላከያ ትልቁ ስኬት በሰላም ጊዜ ከሕዝቡ ጎን በመሰለፍ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ የልማት ምሰሶዎች እውን እንዲኾኑ አበርክቶ ማድረግ መቻሉ ነው። ድንገተኛ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ፈታኝ ወቅትም ቀድሞ በመድረስ ሕዝቡን ይታደጋል።

መከላከያ ሠራዊት ጠላቶች ሲነሱ እንደ ነጎድጓድ ፈጥኖ የሚመክት፣ ሕዝቡ ሲቸገር እንደ እናት እቅፉን የሚከፍት፣ ሰላም ሲሰፍን ደግሞ መሬቱን አርሶ፣ ሀገርን አንጾ የሚያሳድግ የኢትዮጵያ አንድነት ማኅተም እና ዋስትና ነው።

#PeaceAndDevelopment ​#Patriotism #Ethiopia
#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_23_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleአቶ ፀጋው እሸቴ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ተቀዳሚ ዋና አሥተዳዳሪ ኾነው ተሾሙ።
Next articleየቱሪዝም ሕዳሴ በኢትዮጵያ 🇪🇹