“ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሴራ በፅናት ከማክሸፍ ባለፈ በሉዓላዊነቷ አትደራደርም” ዶ/ር ግዛቸው አስራት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተመራማሪ

6
አዲስ አበባ: መስከረም 22/2019(አሚኮ) የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የሕዝቧ አንድነት በውጭ ኃይሎችና ተላላኪዎቻቸው የሚሰነዘርበትን ድል በማድረግ፣ አዲስ የአፍሪካ የብልጽግና ምዕራፍ እየጻፈች ነው።
ግብፅ ባለፉት ዘመናት ሁሉ የኢትዮጵያን ተፈጥሮአዊ የእድገት ጉዞ ለማስተጓጎል እና የተዳከመች ሀገር እንድትኖር የሄደችበት የታሪክ መንገድ የፖለቲካ ሴራው ዋና አካል ነው።
የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተመራማሪ የኾኑት ግዛቸው አስራት(ዶ/ር) ግብፅ በቀጥታ ጦርነትና ወረራ ያልተሳካላትን አላማ ለማስፈጸም፣ የሀገር ውስጥ እና የቀጠናውን ተላላኪ ቡድኖች መጠቀምን እንደ ዋነኛ የውጭ ፖሊሲ ስትራቴጂ ስትከተለው ቆይታለች ብለዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ ጠንካራና የጸና የኢትዮጵያ መንግስት እንዳይመሰረት ስልታዊ የኾኑ በርካታ አካሄዶችን እና እገዳዎችን ስትከተል ቆይታለች የሚሉት ተመራማሪው ዛሬ ግን ኢትዮጵያ ሁሉንም ፈተናዎች አልፋ ጠንካራ፣ የተረጋጋች እና ለአፍሪካ አህጉር በፓን-አፍሪካኒዝም መንፈስ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ተምሳሌት ለመሆን በስኬት መንገድ ላይ ትገኛለች ነው ያሉት።
በቅርቡ የወጡ የጂኦ-ፖለቲካ ትንታኔዎች እንደሚጠቁሙት፣ የኤርትራ ቀጠናውን ለማናጋት የተኪ ኃይሎች ስትራቴጂን በመምረጥ የሃገርን ሉአላዊነት ደፍራለች።
ከአልሸባብ እስከ ሱዳን ጦርነት፣ እንዲሁም በቅርቡ ከህወሓት እና ሌሎች ቡድኖች ጋር የተደረጉ ጊዜያዊና ታክቲካዊ ቅንጅቶች አስመራ ከካርቱም እስከ አዲስ አበባ ያለውን የቀጣና ሁኔታ ለማወክ የተጠቀመችበት መንገድ ነው።
የኤርትራ መንግስትና የግብፅ ፍላጎት በዚሁ ቀጣናዊ ውጥረት ላይ በመገናኘታቸው፣ የኢትዮጵያን የቀይ ባህር እና የድንበር ደህንነት ስጋት ውስጥ የማስገባት አካሄድን መርጠው ተደጋጋሚ የሉአላዊነት ጥሰቶችን ፈፅመዋል።
📈ይህ ዓይነቱ የተቀናጀ የሉአላዊነት ድፍረት የሚመጣው ኢትዮጵያ ቀጠናዊ መሪነቷን እና የኢኮኖሚ አቅሟን እያጠናከረች በመምጣቷ የፈጠረባቸውን ስጋት ለመመከት ከማሰብ የተነሳ ነው ሲሉም ግዛቸው አስራት(ዶ/ር) አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ትላንት ሀገራዊ ሉአላዊነቷን እና የድንበር ደህንነቷን ለማስከበር በግብፅ እና በኤርትራ ላይ የተከተለችው የታጋሽነትና ሰላም ወዳድነት አካሄድ ሙሉ በሙሉ ህጋዊና ተገቢ ነው።
እውነተኛ የሰላም፣ የእድገት እና የአንድነት መንገድ የሚጀምረው ሀገራዊ ሉአላዊነትን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በማክበር እና በጋራ በመቆም ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ኢትዮጵያም ሉአላዊነቴን አላስደፍርም ብላለች።
🇪🇹መላው ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የዓለም ሰላም ወዳዶች የኢትዮጵያን ህጋዊ የሉአላዊነት እርምጃ እና የፅናት ጉዞ በሙሉ አቅማቸው ሊደግፉት ይገባል ብለዋል ተንታኙ።
በኢብራሂም መሃመድ
Previous articleየግብጽ ሴራ እና የኢትዮጵያ ጽናት
Next articleበዲጂታል ኢኮኖሚው የሴቶችን ተሳታፊነት የሚያሳድግ መርሐግብር በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተጀመረ።