
ግብጽ ታሪካዊ ጠላትነቷን በማወጅ ኢትዮጵያን ለማተራመስ፣ ለመከፋፈል እና ሉዓላዊነቷን ለመገዳደር አፍራሽ ሴራዎችን ስትጎነጉን ቆይታለች።
ኤርትራም በዚሁ ድጋፍ በመተማመን ተላላኪነቷን አጠናክራ ቀጥላለች። የዚህ ሁሉ ውጥረት ማዕከል የዓባይ ወንዝ እና የቀይ ባህር ጂኦፖለቲካዊ ጥቅም ሲኾን የሁለቱ አካላት ጥምረት ዋና ዓላማ የራሳቸውን የበላይነት ለማረጋገጥ ሲሉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ መጣል ነው።
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ፍልስፍና መምህር ዓለምነህ አጋዤ እንደሚገልጹት ግብጽ የናይልን ውኃ እንደ ብቸኛ የህልውና ጉዳይ በመመልከት የኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴዎች በስጋትነት ትፈርጃለች።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እውን እንዳይኾንም ከዓለም አቀፍ ጫና እስከ ፕሮፓጋንዳ እንዲሁም በትምህርት ሥርዓቷ ጥልቅ ሃሳቦችን አካታ የተጣመመ እይታ ያለው ትውልድ እስከ መቅረጽ ሠርታለች።
በተጨማሪም ሻቢያን ከመደገፍ እና ኤርትራን ከኢትዮጵያ የመገንጠል ሂደት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ኤርትራን ከጎኗ በማሰለፍ የዓባይን ወንዝ እና የቀይ ባሕርን ተደራሽነት ለመቆጣጠር እየሠራች ትገኛለች።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በታሪክ የተቃጡባትን ወረራዎች እና የእጅ አዙር ሴራዎች በድል በማክሸፍ ሉዓላዊነቷን ስትጠብቅ ኖራለች። ዛሬም ቢኾን የሚሰነዘሩባትን ጫናዎች ለመመከት በሰከነ ዲፕሎማሲ፣ በማደግ ላይ በሚገኝ ኢኮኖሚ እና ዘመናዊ ትጥቅ ባለው ብቁ የመከላከያ ሠራዊት አቅሟን እያጠናከረች ትገኛለች።
በመኾኑም የሀገርን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሕዝብ አንድነት እና መተባበር ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያ ለጠላቶቿ ያልተንበረከከ ታሪኳን በማስቀጠል የቀጣናውን ሰላም እያረጋገጠች እና የውስጥ እንዲሁም የውጭ ጫናዎችን እየመከተች ወደ ታላቅ ከፍታ ጉዞዋን ትቀጥላለች።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
