
ኢትዮጵያ የራሷን የነፃነት እና የሉዓላዊነት ህልውና አስከብራ ከመኖር ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት መረጋጋት፣ ለአህጉራዊ ነፃነት እና ለዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ግንባር ቀደም አለኝታ ኾና የዘለቀች ሀገር ናት። ይህ ቀናና በጎ አጎራባችነቷ ግን ጥንትም ኾነ ዛሬ ያልተዋጠላቸው ጥቂት የጎረቤት ሀገራት በሉዓላዊነቷ እና በግዛት አንድነቷ ላይ አላስፈላጊ ትንኮሳዎች ሲሰነዘሩባት ይስተዋላል።
ታሪክ ዘልቆ የሚናገረው አንድ የማይቀየር እውነት ግን አለ። ኢትዮጵያ ጥንካሬዋን እና ሉዓላዊነቷን አሳልፋ የማትሰጥ ሀገር መኾኗ። በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በኋላም በሱዳን እና በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የከፈለችው መስዋዕትነት የሰላም ማስከበርና የቀጣናው አለኝታነቷን በተግባር ያረጋገጠ ነው።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃነት ላይም ያላት አበርክቶ በጉልህ የሚጠቀስ ነው። አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ቀንበር እንዲላቀቁ የደቡብ አፍሪካን፣ የዚምባብዌን እና የሌሎችንም ንቅናቄዎች በመደገፍ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ አፍሪካ ኅብረት) መሠረት እንዲጣል አድርጋለች።
ደራሲ እና የታሪክ ተመራማሪ ቹቹ አለባቸው “የተከዜ ፖለቲካ ” በተሰኘው አዲስ መጽሐፋቸው እንዳመላከቱት ኢትዮጵያ በታሪኳ ለውጭ ወረራ እና ትንኮሳ የምትጋለጠው የውስጥ አለመግባባቶች እና የፖለቲካ ክፍተቶች በሚፈጠሩበት ወቅት እንደኾነ ገልጸዋል።
አሁን ላይ እየኾነ ያለውም ይሄው ነው። ግብጽ እና ኤርትራ የኢትዮጵያን የውስጥ ችግር እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የድንበር መድፈር እና የታሪካዊ መብቶች ጥሰት ለማድረስ እንደሚሞክሩ ጠቅሰዋል። ኾኖም ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገር ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ ልዩነቶቹን ወደ ጎን በማለት በአንድነት የመቆም ተፈጥሯዊ የታሪክ ባሕል እንዳለው አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ የሰላም፣ የትብብር እና የጋራ ዕድገት ፈላጊ ሀገር ናት። የሀገርን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ክብር የማስከበር ጉዳይ ሲመጣ ግን ድርድር የሌለው እና የማይታጠፍ የአቋም ጥንካሬ አላት። ኢትዮጵያ ትናንትም ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረች ሀገር ናት።
የጎረቤት ሀገራት ከቀደመ ታሪክ ተምረው የሰላምን እና የጋራ ዕድገትን መንገድ መምረጥ ግን ወሳኙ ጉዳይ ይኾናል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ
