
የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት ሰባተኛ ዙር አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን መሥራች የሁለተኛ ቀን ጉባኤውን አካሂዷል።
ምክር ቤቱ በሁለተኛ ቀን ጉባኤው የአማራ ክልል መንግሥት የ2019 በጀት ዓመት የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድን ገምግሟል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉ መንግሥት የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ፕሮጄክቶች እንዲጠናቀቁ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
በክልሉ ከፍተኛ የኾነ የመሠረተ ልማት ፍላጎት እንዳለም ተናግረዋል። ለመሠረተ ልማት የተያዘው በጀት እና ፍላጎቱ ግን ከፍተኛ እርቀት እንዳለው ነው የተናገሩት።
በአቅም እና በፍላጎት መካከል ያለውን ርቀት ማጣጣም እንደሚያስፈልግም አንስተዋል። የክልሉ መንግሥት ትልልቅ የልማት ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል ዕቅድ ማቀዱንም ገልጸዋል። በኢንዱስትሪ፣ በመሠረተ ልማት፣ በማዕድን እና በግብርና ዘርፍ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ሥራዎች እንደሚሠሩም አንስተዋል።
የትምህርት ዘርፉን ለማሻሻል ሞዴል ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ መያዛቸውንም ገልጸዋል። በሁሉም መስክ በዕቅድ የተያዙ ፕሮጄክቶች የሚፈልጉት በጀት ከፍተኛ መኾኑንም አንስተዋል።
ፕሮጄክቶችን የምንመራው በአዋጭነት እና በፍትሐዊነት መርሕ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ አንዳንድ ፕሮጄክቶች በአዋጭነት ይሠራሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በፍትሐዊነት ይሠራሉ ነው ያሉት። ተጀምረው ያደሩ ፕሮጄክቶችን ለቅመው መያዛቸውንም አመላክተዋል።
ከመሠረተ ልማት ግንባታ ባሻገር የተሠሩ ልማቶችን መጠበቅ እና መንከባከብ እንደሚገባም አንስተዋል። በመሠረተ ልማት ላይ የሚደርሰውን ስርቆት እና ውድመት መቆጣጠር ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ተሠርቷል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ አሁንም ተማሪዎች በተሟላ ሁኔታ እንዲመለሱ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ማኅበረሰቡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ እንዲያግዝም ጠይቀዋል።
ሁሉንም ልማት የሚያንቀሳቅሰው የሰው ኀይል ነው፤ የሰው ኀይሉን ውጤታማ ለማድረግ ደግሞ ውጤታማ ሥራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት። ለመሠረተ ልማት የሚከፈለውን የካሳ ክፍያ የተጋነነ አድርጎ የማቅረብ ችግርን መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ሀገረ መንግሥቱን የሚያጸና እና ወንድማማችነትን በሚያጠናክር መልኩ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ አንስተዋል። ለመሥራት የታቀዱ ፕሮጄክቶች በማኅበረሰብ ተሳትፎ እንዲሠሩ ምክር ቤቱ እገዛ እንዲያደርግም ጠይቀዋል። ምክር ቤቱ ሥራዎችን ሲገመግም፣ ሲከታተል እና ሲጠይቅ ዕቅዱን መሠረት በማድረግ እንዲኾንም ጠይቀዋል።
አስፈጻሚ አካሉ በሚሠራው ሥራ ለመጠየቅ ዝግጁ መኾኑንም አስታውቀዋል። “የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጋራ እንሥራ”ም ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
