
በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና እየተስተዋለ ያለው ፈጣን እና ውስብስብ የጂኦፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የካይሮን የቆየ እና ያረጀ የሴራ ፖለቲካ እንደገና በግልጽ ፍንትው አድርጎ ያሳየ ነው።
ግብጽ የምሥራቅ አፍሪካን ደኅንነት ለማወክ የምታደርገው ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ የእጅ አዙር ጣልቃ ገብነት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት የተደረገ ሳይኾን ኢትዮጵያ ያነሳችውን ብሔራዊ የባሕር በር አጀንዳ እና የጀመረችውን ሁለንተናዊ የልማት ጉዞ ለማደናቀፍ ያለመ ነው።
የካይሮ የፖለቲካ ልሂቃን ኢትዮጵያ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ይዛ፣ የተፈጥሮ ሀብቷን ተጠቅማ እና በቀይ ባሕር አካባቢ ተጽዕኖ ፈጣሪ ኾና እንድትወጣ አይፈልጉም። በየዘመኑ የውስጥ አጥፊዎችን እና ባንዳዎችን በፍርፋሪ በመደለል ኢትዮጵያን የመውጋት ሥራቸውን ዛሬም እንደትናንቱ አስቀጥለው ይስተዋላሉ።
ይህንን እውነታ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሃጋይ ኤርሊክ ዘ ክሮስ ኤንድ ዘሪቨር (The Cross and the River) በተሰኘው መጽሐፋቸው “የካይሮ ስሌት ግልጽ ነው፤ ኢትዮጵያን የባሕር በር አልባ ማድረግ የሰርክ ግቧ ነው ሲሉ አስፍረዋል። ይህንን ለማሳካት ደግሞ የኢትዮጵያ ልጆች የኾኑትን፤ ነገር ግን የባንዳነት ሥነ ልቦና የተጠናወታቸውን ግለሰቦች እና ቡድኖች በፍርፋሪ እየገዙ ማሰለፍ ዋነኛው ስልታቸው ነው” ይላሉ።
ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ Ethiopia and the Nile: Dilemmas of Sharing በሚለው ጥናታቸው የግብጽ አካሄድ ከሳይንሳዊ እና ከዓለም አቀፍ የፍትሕ መርሆዎች ያጋደለ፣ የ1959ኙን የቀኝ ግዛት የውኃ ክፍፍል የበላይነት በ21ኛው ክፍለ ዘመን በጉልበት ለመጫን ያለመ ስግብግብነት ነው ሲሉ አትተዋል።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የዓባይን ውኃ በብቸኝነት በመቆጣጠር እና ኢትዮጵያን በውስጥ ግጭቶች በመጥመድ ከቀይ ባሕር ቀጣና ለማግለል ያለመ ቢኾንም ኢትዮጵያ ግን በልማት፣ በሰላም እና በቀጣናዊ ትስስር አዲስ እውነታን እያረጋገጠች ትገኛለች፤ አጠናክራ ትቀጥላለችም።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ 
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
