
ዕቅዱ ክልሉን በሁለንተናዊ መንገድ ሊያሻግር የሚችል ነው። የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት ሰባተኛ ዙር አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመሥራች ሁለተኛ ቀን ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
ምክር ቤቱ በሁለተኛ ቀን ጉባኤው የአማራ ክልል መንግሥት የ2019 በጀት ዓመት የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድን እየገመገመ ነው።
የአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ኀላፊ ደመቀ ቦሩ (ዶ.ር) የታቀደውን ዕቅድ በተገቢው መንገድ መፈጸም ከተቻለ ክልሉን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር መኾኑን ገልጸዋል። ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም በትኩረት መሥራት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል። ዕቅዱ ክልሉን በሁለንተናዊ መንገድ ሊያሻግር የሚችል መኾኑንም ገልጸዋል።
ዕቅዱ ውጤታማ እንዲኾን የምክር ቤት አባላትም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባቸው አመላክተዋል። የምክር ቤት አባላቱ ጥናታቸው የተጠናቀቁ እና ሥራ የጀመሩ ትልልቅ የመስኖ ፕሮጄክቶችን መሥራት እንደሚገባውም አንስተዋል።
የፌዴራል ፕሮጄክቶች እንዲጠናቀቁ ማድረግ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። የመንገድ ደኅነትን ማስጠበቅ፣ የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎችን መፍታት እንደሚገባም አመላክተዋል።
ግብርናውን ውጤታማ ለማድረግ የግብዓት አቅርቦትን ቀልጣፋ እና ፍትሐዊ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። የክልሉን ሰላም እና ደኅንነት ማረጋገጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መኾኑንም ገልጸዋል።
የመብራት፣ የመንገድ እና የቴሌኮም ተደራሽነት ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ማየት እና ጥያቄዎችን መፍታት እንደሚገባም አመላክተዋል።
የታቀደውን ዕቅድ በውጤታማነት ለመተግበር በቅንጅት እና በትብብር መሥራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
