
”ችግር ፈቺ መሪዎችን በማፍራት ክልሉን ከድኅነት አዙሪት ለማውጣት ይሠራል”
የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት ሰባተኛ ዙር አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን መሥራች ጉባዔ የሁለተኛ ቀን ውሎውን እያካሄደ ነው።
ምክር ቤቱ በሁለተኛ ቀኑ ጉባኤው የአማራ ክልል መንግሥት የ2019 በጀት ዓመት የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድን እየገመገመ ይገኛል።
ዕቅዱን ያቀረቡት የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ ኀላፊ ደመቀ ቦሩ ( ዶ.ር) በትምህርት ዘርፉ ጥራት፣ ፍትሐዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ፤ ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት እና የተማሪዎችን የማለፍ ምጣኔ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የትምህርት ፍትሐዊነት እና አካታችነትም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል። ለመምህራንም ሥልጠና እንደሚሰጥ አመላክተዋል። የመማሪያ ቁሳቁሶችን የማሻሻል እና ግብዓቶችን የሟሟላት ሥራ ይሠራል ነው ያሉት። የጎልማሶች ትምህርት እና መደበኛ ያልኾኑ ትምህርቶች ትኩረት እንደሚሠጣቸውም አንስተዋል።
የቀዳማይ ልጅነት እና የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ውጤታማ እንዲኾን ይሠራል ብለዋል። የተማሪዎች ምገባም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል።
በችግር የማይበገር የጤና ሥርዓት ለመፍጠር እና ጤናማ ዜጋ ለመገንባት በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት። የምግብ ሥርዓትን የማሻሻል፣ የእናቶች እና የሕጻናት ጤና ላይ ትኩረት ይደረግበታልም ብለዋል። ተላላፊ የኾኑ በሽታዎችን የመከላከል እና ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች በማኅበረሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ትኩረት የማድረግ ሥራ እንደሚከናወንም ገልጸዋል።
ማኅበራዊ ፍትሕን የማረጋገጥ ሥራም በትኩረት እንደሚሠራበት አመላክተዋል። ለዜጎች የማኅበራዊ ድጋፍም እንደሚደረግ ነው የተናገሩት። ማዕድ ማጋራትም በልዩ ኢንሼቲቭ እንደሚተገበር አንስተዋል።
ከተሞችን የማልማት፣ የተጠናከረ የከተማ ገጠር ትስስር፣ የከተማ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሥራ ይሠራል ነው ያሉት። የከተማ ኮሪደር ልማት ሥራም ትኩረት የሚደረግበት መኾኑን ገልጸዋል። ዘመናዊ የገጠር መንደሮች እንዲገነቡም ይሠራል ነው ያሉት።
ዕቅዶችን በተገቢው መንገድ ለመተግበር የቴክኖሎጂ አቅምን እንደሚጠቀሙ አንስተዋል። ቴክኖሎጂን የተላመደ ማኅበረሰብ መገንባት፣ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶችን ማልማት ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ እንደሚስፋፋም ገልጸዋል። ዕቅዶችን ለመተግበር የሰው ኃይልን በአግባቡ እንደሚጠቀሙ ነው የተናገሩት። ምሁራን በክልሉ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ይሠራል ብለዋል።
የመሬት ሃብትን በአግባቡ እንደሚጠቀሙም ገልጸዋል። የክልሉን መዋዕለ ነዋይ ለማሳደግ እንደሚሠራ ተናግረዋል። ዕቅዶችን ለማሳካት የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ማረጋገጥ የሕግ ማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል። የባሕል እሴት ግንባታም ትኩረት ይሠጠዋል ነው ያሉት።
”ጠንካራ እና ችግር ፈቺ መሪዎችን በማፍራት ክልሉን ከድኅነት አዙሪት ለማውጣት ይሠራል” ነው ያሉት። የተቋማትን የመፈጸም እና የማሥፈጸም አቅም እናሳድጋለንም ብለዋል። ፕሮጄክቶች ጠንካራ ክትትል እና ቁጥጥር እንደሚደረግባቸውም አንስተዋል።
#ባሕር_ዳር #መስከረም_22_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
