
“ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው” ደመቀ ቦሩ (ዶ.ር) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት ሰባተኛ ዙር አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን መሥራች የሁለተኛ ቀን ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
ምክር ቤቱ በሁለተኛ ቀን ጉባኤው የአማራ ክልል መንግሥት የ2019 በጀት ዓመት የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድን እየገመገመ ነው።
ዕቅዱን ያቀረቡት የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ ኀላፊ ደመቀ ቦሩ ( ዶ.ር) ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መኾኑን ገልጸዋል። የክልሉ እሴቶችን መገንባት፣ ለዘላቂ ሰላም እና ልማት መጠቀም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ እንደኾነ ነው ያነሱት።
ዘመናዊ ግብርና፣ ማዕድን፣ ኢንዱስትሪ፣ ዘመናዊ ቱሪዝም፣ ቴክኖሎጂ ግንባታ ትኩረት የሚሰጣቸው ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች መኾናቸውን አንስተዋል።
ምርት እና ምርታማነትን መጨመር፣ የኑሮ ውድነትን መቀነስ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠርም በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት። በክልሉ 10 ነጥብ 2 በመቶ አጠቃላይ ዕድገት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል።
ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በማሳደግ ከውጭ ምንዛሬ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እንሠራለንም ነው ያሉት። በቱሪዝም ዘርፉ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ወደ ክልሉ በስፋት እንዲመጡ እና የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም እንሠራለን ነው ያሉት። የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን ወደ ክልሉ መሳብ እና የቆይታ ጊዜያቸውን ማራዘም የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
አምራች ኢንዱስትሪው ውጤታማ እንዲኾን እና አሁን ካለው የተሻለ ዕድገት እንዲኖረው ይሠራል ነው ያሉት። የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሳደግ ላይ ትኩረት እንደሚደረግም አመላክተዋል። ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እንደሚገነባም ገልጸዋል። የኢንዱስትሪ የማምረት አቅምን ወደ 70 በመቶ ለማሳደግ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
ግብርናውን ለማዘመን ይሠራል ያሉት ኀላፊው በምግብ ራሳችን እንችላለን፣ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ለውጥም እናመጣለን ነው ያሉት። ለፋብሪካ ግብዓት የሚኾኑ ምርቶችንም በስፋት እናመርታለን ብለዋል።
የግል ባለሀብቶችም በግብርናው ዘርፍ እንዲሠማሩ እና የሜካናይዜሽን ልማት እንዲሠፋ ይሠራል ብለዋል። ከእንስሳት የሚገኘውን ሃብት የበለጠ ለማሳደግ ለሌማት ትሩፋት ትኩረት እንደተሰጠውም ነው የተናገሩት።
የማዕድን ሃብቱን በአግባቡ ለመጠቀም በጥናት ሃብቱን የመለየት ሥራ ይሠራልም ብለዋል። ዘመናዊ የማዕድን ላቦላቶሪ ለመገንባት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማስፋት፣ የማልማት እና የጎብኘዎችን ቁጥር የመጨር ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል። ባሕላዊ ምግቦች እና መጠጦች በሆቴሎች እንዲቀርቡ እና የሚገባቸውን ኢኮኖሚ እንዲያመነጩ የማስቻል እና የመዳረሻ ቦታዎችን የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራልም ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
