
ለሰላም እና ልማት ግንባር ቀደም እንደሚኾኑ የደብረ ታቦር ከተማ ወጣቶች ገልጸዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ ወጣቶች “ለከተማችን ሰላም እና ልማት ግንባር ቀደም ዘብ እንቆማለን!” በሚል መሪ መልእክት ተወያይተዋል።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉት ወጣቶች ከአካባቢያቸው የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሰላማቸውን እየጠበቁ ለልማት እንደሚተጉ ገልጸዋል።
አሁን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል የሰላም ዘብ በመኾን፣ የንግድ እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እንዳይስተጓጎሉ በማድረግ እና በመረጃ ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማሳየት የከተማቸውን ልማት በቁርጠኝነት ለማፋጠን ዝግጁ መኾናቸውን አረጋግጠዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኃይለኢየሱስ ሰለሞን የሀገር ዕድገት እና ዘላቂ ለውጥ ሊረጋገጥ የሚችለው በወጣቶች የነቃ ተሳትፎ መኾኑን ገልጸዋል።
ወጣቶች ሰላም እና ጸጥታን በማረጋገጥ አሁን ለተገኘው አንፃራዊ ሰላም ከፍተኛ ድርሻ ማበርከታቸውን ጠቁመው በቀጣይም እነዚህን አርዓያነት ያላቸው ተግባራት በላቀ ሁኔታ ለመፈጸም የከተማ አሥተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በውይይት መድረኩ ማጠቃለያ ላይ የተጀመረውን አንድነት በማስቀጠል ሰላምን የማጽናት እና በልማት ሥራዎች ላይ የወጣቶች ድርሻ የላቀ እና ተስፋ ሰጭ መኾኑ ተመላክቷል።
ዘጋቢ:- ተክለብርሃን ፈንታ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
