የኢትዮጵያ የሰላም ፍላጎት፤ ከቃላት ባለፈ በተግባር ሲመዘን ! “ሁለት ዓመት ከመዋጋት 20 ዓመት መወያየት ይሻላል”
የኢትዮጵያ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ፖሊሲ ማጠንጠኛ የኾነው ሰላም በቃላት ብቻ ሳይኾን በተጨባጭ ተግባር እና መዋቅራዊ አደረጃጀት የሚገለጽ የሀገሪቱ የሕልውና መሠረት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በ2015 ዓ.ም በነበረ የሰላም መድረክ ላይ “ሁለት ዓመት ከመዋጋት 20 ዓመት መወያየት ይሻላል” በማለት የኢትዮጵያ ቀዳሚ መሻት ሰላም እና መረጋጋት መኾኑን አረጋግጠዋል። ሀገሪቱ ይህንን የሰላም እሴት በውስጣዊ ጉዳዮቿም ኾነ በቀጣናዊ ግንኙነቷ በተግባር እያዋለችው ትገኛለች።

ውይይት እና እርቅን ያስቀደመ ውስጣዊ መረጋጋት ኢትዮጵያ ውይይትን እና እርቅን እንደ ዋነኛ መሣሪያ አድርጋ ትጠቀማለች። የመንግሥት ጽኑ አቋም “ችግሮቻችንን በጠመንጃ እና በጉልበት ሳይኾን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት እና በመቻቻል መፍታት ይኖርብናል” የሚል ነው። ይህም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያጋጠሙ የትጥቅ ትግሎች ወደ ሰላማዊ የትግል መንገድ እንዲገቡ አስችሏል።

ለብሔራዊ መግባባት የተዘረጋ ተቋማዊ ግንባታ፦ ከግጭት አፈታት ባሻገር ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ ሥር የሰደዱ እና ለዘመናት የዘለቁ ሀገራዊ ቁርሾዎችን ከመሠረቱ መፍታት አስፈላጊ መኾኑ ታምኖበታል። ይህም አንዲት የጋራ ሀገርን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመገንባት የተያዘውን ሀገራዊ ቁርጠኝነት በተጨባጭ የሚያረጋግጥ ነው።

“ቅድሚያ ለጎረቤት” – ከድንበር የተሻገረ ቀጣናዊ ርዕይ፦ በሀገር ውስጥ የተጀመረው ይኸው የሰላም ግንባታ ጥረት ከድንበር ባሻገርም “ቅድሚያ ለጎረቤት” በሚለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ደምቆ ይታያል። የጎረቤት ሀገራት ሰላም መኾን ለኢትዮጵያ ሰላም ዋስትና መኾኑን በመገንዘብ ሀገሪቱ የአፍሪካ ቀንድን የሰላም እና የመረጋጋት ማዕከል ለማድረግ በጽናት እየሠራች ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የጎረቤቶቻችን ሰላም የኛም ሰላም ነው፤ ጎረቤቱ ሰላም ያጣ እና የተራበበት ሀገር ለብቻው ሰላማዊ እና ባለጸጋ ሊኾን አይችልም” በማለት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ለቀጣናው ደኅንነት የላቀ ሚናዋን እየተወጣች ነው።

ለሰላም ማስከበር የሚከፈል ተግባራዊ መስዋዕትነት፦ ይህ ቀጣናዊ ርዕይ በፖሊሲ ሰነድ ላይ ብቻ የቆመ ሳይኾን በተግባር የተፈተነ ነው። ለዚህም በሶማሊያ አሸባሪነትን ከመዋጋት ጀምሮ በታሪክም በኮንጎ እና በሌሎችም የተለያዩ የዓለም ክፍል የተሰማራው ሰላም አስከባሪ ኅይል፣ ቀዳሚ ማሳያዎች ናቸው።

ሰላምን በጋራ የኢኮኖሚ ትስስር ማጽናት፦ ከፖለቲካዊ እና ጸጥታ ማስከበር ውጥኖች ባለፈ ኢትዮጵያ ይህን ሰላም የማጽናት ጥረት ከጋራ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በጥብቅ አቆራኝታዋለች።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የመንገድ፣ የባቡር እና የኤሌክትሪክ ኀይል ማስተላለፊያ መሠረተ ልማቶችን ከጂቡቲ፣ ኬንያ እና ከሌሎችም ጎረቤት ሀገራት ጋር በማስተሳሰር ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደት እንዲፈጠር ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተጫወተች ነው።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ! በአጠቃላይ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚደረገው ተቋማዊ ጥረት፣ ለጎረቤት ሀገራት ሰላም የሚከፈለው መስዋዕትነት እና የኢኮኖሚ ትስስርን ለመፍጠር የሚሠራው ስትራቴጂካዊ ተግባር ሲደመሩ አንድ ሐቅን ያወጣሉ።
ይኸውም ከትልቅ ሀገር እና ከትልቅ ሕዝብ በሚመነጭ ታላቅ ርዕይ ኢትዮጵያ ሰላምን የህልውናዋ መሠረት እና የቀጣናው የብርሃን ማማ አድርጋ ዘላቂ ጉዞዋን አጠናክራ ቀጥላለች።

በስማቸው አጥናፍ