
የኢትዮጵያ ሰላማዊ የባሕር በር መሻት። የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከትልቅ ሀገር እና ከትልቅ ሕዝብ የጋራ ብልጽግና እሳቤ የሚመነጭ ታላቅ ርዕይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት እና በቀይ ባሕር እንዲሁም በዓባይ ወንዝ መካከል የምትገኝ ሀገር ያለ ባሕር በር መቅረቷ በዓለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ እና የማይቻል ሀቅ ነው ብለዋል።
የባሕር በር መሻቱ ከምንም በላይ ጥልቅ የኾነ ኢኮኖሚያዊ አስፈላጊነት ያለው ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናት እንደሚያሳየው የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርታቸው ከ25 በመቶ እስከ 30 በመቶ የሚኾነውን ለባሕር በር አገልግሎት እና ለትራንዚት ወጭ ያውላሉ።
የባሕር በር እንደ ትልቅ እና እያደገ ያለ ኢኮኖሚ፣ አስተማማኝ እና የተለያየ የዓለም አቀፍ ንግድ መስመሮች ተደራሽነት ለኢትዮጵያ እጅግ ወሳኝ ነው።
ርዕዩን ለማሳካት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብሪክስ ጉባኤ አቋማቸውን በግልጽ አስቀምጠዋል፤ “ዓላማችን የንግድ ወጭዎችን መቀነስ፣ የበለጠ የመቋቋም አቅምን መገንባት እና የጋራ ብልጽግናን ማሳደግ ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ይህን የህልውና ጉዳይ በሰላማዊ እና በድርድር በሚደረሱ ስምምነቶች ማሳካቷን እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል። ከትልቅ ሀገር እና ሕዝብ የሚመነጨው ይህ ጠንካራ አቋም ሀገሪቱ ያላትን ርዕይ ዕውን ለማድረግ የጎረቤቶቿን ሉዓላዊነት አጥብቃ የምታከብር፣ በሰላማዊ ድርድር እና በቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር ላይ ብቻ እምነት ያላት መኾኗን በተጨባጭ የሚያሳይ ነው።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
