ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ!

4

 

“የክልሉ መንግሥት የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ልዩ ትኩረት ይሰጣል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት ሰባተኛ ዙር አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን መሥራች ጉባዔውን እያካሄደ ነው።

ምክር ቤቱ አቶ አረጋ ከበደን የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አድርጎ በድጋሜ ሾሟል።

ከሹመታቸው በኋላ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉን ኢኮኖሚ ለሚያሻሽሉ ሥራዎች ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል። ለአምራች እንዱስትሪው እና ለዘመናዊ ግብርና ትኩረት እንደሚሠጥም ገልጸዋል። ቴክኖሎጂ መር ግብርና እንደሚተገበርም ተናግረዋል።

የተቀናጀ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል። ዜጎች የተሻለ አኗኗር እንዲኖሩ ይሠራል ነው ያሉት። ዘመናዊ መስኖ ልማትን መሠረት ያደረገ ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪውን ውጤታማ ለማድረግ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እንደሚቋቋም ነው ያነሱት። የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ክልሉ እንዲመጡ በትኩረት እንደሚሠራም አመላክተዋል።

የክልሉን የማዕድን ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም ከፍተኛ ትኩረት እንደሚደረግበት አንስተዋል። የማዕድን ጥራትን እና ክምችትን መሠረት ያደረገ የልማት ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል። ተወዳዳሪ የማዕድን እንዱስትሪ እንዲኖር ይሠራል ነው ያሉት።

ሕገ ወጥ የማዕድን ዝውውርን በመግታት ተጨባጭ እና ውጤታማ ሥራ እንደሚሠራ አመላክተዋል። ለክልሉ የቱሪዝም ሃብትም ልዩ ትኩረት እንደሚሠጠውም ገልጸዋል። ክልሉ እምቅ የቱሪዝም ሃብት ባለቤት እንደኾነ ተናግረዋል። የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማስፋፋት እና አገልግሎትን የማዘመን ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።

ትምህርት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማምጣት እና ድህነትን ለማስወገድ ወሳኝ ጉዳይ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ባለፉት ዓመታት በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ ነገር ግን በሚፈለገው ደረጃ ስኬታማ ሥራ አልተሠራም ነው ያሉት። በተለይም በክልሉ ተፈጥሮ የቆዬው የጸጥታ ችግር የትምህርት ዘርፉን ጎድቶ ቆይቷል ብለዋል።

እነዚህን ማነቆዎች ለመሻገር በትኩረት እንደሚሠራ ነው የተናገሩት። ትምህርት ለአምራች እንዲስትሪው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ትኩረት ይደረግበታል ነው ያሉት። ሞዴል ትምህርት ቤቶች እንዲገነቡ እና ጥራትን መሠረት ያደረገ ሥራ እንዲሠሩ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት በጤናው ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን ተናግረዋል። የእናቶች እና የሕጻናት ሕክምና እንዲሻሻሉ መደረጉን ገልጸዋል። የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁስ ተደራሽነት ላይ በትኩረት መሠራቱንም ተናግረዋል። የጤናው ዘርፍ አሁንም ፈታኝ ሥራዎች አሉበት ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ፈተናዎችን የሚሻገር ሥራ ለመሥራት በትኩረት እንደሚከናወን ገልጸዋል።

የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ሽፋን እንዲያድግ እና የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሻሻል በትኩረት ይሠራል ብለዋል። በጤናው ዘርፍ ምርምር እንዲጠናከር እንደሚሠራም ተናግረዋል።

ዜጎች ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ እንደሚሠራም ተናግረዋል። ክልሉ በርካታ ሠሪ ኃይል ያለው ነው ብለዋል። ይሄን ሠሪ ኃይል በአግባቡ መጠቀም እና ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

የሰው ኃይልን በማሠልጠን ሰብዓዊ ሃብታችንን በአግባቡ እንጠቀማለን ብለዋል። የሰው ኃይል ልማቱን ውጤታማ የሚያደርግ የሥስልጠና ማዕከል እንደሚኖርም ገልጸዋል።

ተቋማት በሰው ኃይል ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩም አስገንዝበዋል። መሠረተ ልማት እንዲስፋፋ እና ለክልሉ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ይሠራል ነው ያሉት።

የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች የተቀናጁ እና ጥራት ያላቸው እንዲኾኑ እንደሚሠራ ተናግረዋል። የመሠረተ ልማት ፍትሐዊነት፣ ፍጥነት እና ጥራት እንዲረጋገጥ በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።

በዘርፉ የሚፈጠረውን ብልሹ አሠራር እንዳይኖር እንደሚሠራ ገልጸዋል። የተቋም ግንባታ እና የፋይናንስ አቅም ማሳደግ ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት እንደሚሠራ አንስተዋል። ሕዝብ ያማረሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት እንደሚደረግም ገልጸዋል። ዜጎች ከእንግልት የሚወጡበት ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲኖር ይሠራል ነው ያሉት። ግልጽነት የጎደለው እና ቀርፋፋ የአገልግሎት አሠጣጥ እንዲሻሻል ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።

ዜጋን መሠረት ያደረገ የአገልግሎት አሠጣጥ ለመፍታት እንደሚሠራም ተናግረዋል። የአገልግሎት አሰጣጥን ለመፍታት በሚደረገው ሂደት ምክር ቤቱ እንደሚደግፍ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ሙስና የሕዝብ እድገት ጠንቅ መኾኑን በመረዳት መሥራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ_ኢትዮጵያ 🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_21_2019_ዓ_ም

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article‎#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ