
የ25 ዓመታት ርዕይ ማሳካትን ግብ ያደረገው አዲሱ የአማራ ክልል መንግሥት
በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት የተከሰተውን ውስጣዊ አለመረጋጋት በመቀልበስ ለሰላም ግንባታ ትኩረት ሰጥቶ ተሠርቷል። በዚህም ክልሉን ከተጋረጠበት ሁለንተናዊ ቀውስ ለማውጣት ከሕዝብ ጋር በተደጋጋሚ በመምከር የተሻለ ሰላም ማምጣት ተችሏል።
በተጨማሪም የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ፣ አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲሠሩ በርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የሚመራው የክልሉ መንግሥት ሰፊ ተግባር ሲያከናውን ቆይቷል። በዚህም ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን በክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 12ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ መነሳቱ ይታወሳል።
የክልሉ መንግሥት ያለፈውን የታሪክ ሂደት ተንትኖ፣ ወቅቱን ቃኝቶ፣ ነገን አልሞ፣ ክልሉን የሚያሻግር፣ ለመጭው ትውልድ የሚተርፍ የአምስት ዓመታት ስልታዊ ዕቅድ እና የ25 ዓመታት የልማት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ወደ ተግባር ገብቷል።
ዛሬ የተመሠረተው አዲሱ የክልሉ መንግሥትም ቀደም ብሎ የተዘጋጀውን የ25 ዓመታት የልማት ፍኖተ ካርታን ግብ ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ተመላክቷል። ለዚህም ለክልሉ የመልማት አቅም መሠረት የኾኑ የፋይናንስ አቅምን የማሳደግ እና የተቋም ግንባታ ሥራን በትኩረት እንደሚሠራ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ተናግረዋል።
አዲስ የተመሠረተው መንግሥት በቀጣይ የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ትኩረት ሰጥቶ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አመላክተዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ በክልሉ የመንግሥት ምሥረታ ወቅት እንደተናገሩት በቀጣይ በክልሉ የፖለቲካ መረጋጋት እንዲመጣ፣ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ የተጀመሩት የፖለቲካ እና የሕግ ማስከበር ሥራዎች ውጤታማ እንዲኾኑ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።
ሰላምን በማጽናት ክልሉ ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ ጠንክሮ እንደሚሠራም ገልጸዋል። በተቋማት የሚሠጡ አገልግሎቶችን ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና ከብልሹ አሠራር የጸዱ በማድረግ የሕዝብ እንግልትን ለመቀነስ በቁርጠኝነት ይሠራል ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ። እርስዎስ በዚህ ጉዳይ ምን አስተያየት አለዎት? በሀሳብ መስጫው ያጋሩን 👇
#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ_#ኢትዮጵያ 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_21_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
