የመስኖ ልማት እና የአርሶ አደሮች ተስፋ በሲያደብር እና ዋዩ ወረዳ!

5

 

በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን ሲያደብር እና ዋዩ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች የድካማቸውን ፍሬ ለማየት ሌት ተቀን እየጣሩ ይገኛሉ።

የበጋ መስኖ ልማትን እንደ መልካም ዕድል በመጠቀም በኑሮአቸው ላይ አዎንታዊ ለውጥ እያመጡ ካሉት መካከልም አርሶ አደር ወንደሰን ደሴ ይጠቀሳሉ።

ባለፉት ዓመታት በበጋ መስኖ ልማት ውስጥ በመሳተፍ አጥጋቢ ምርት ማግኘታቸውን የሚገልጹት አርሶ አደር ወንደሰን በዚህ ዓመትም አራት ሄክታር መሬታቸውን በበጋ መስኖ ለማልማት አሁን ላይ የማለስለስ ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ።

ለዚህም ሥራ የሚኾን በቂ ምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት እያገኙ መኾኑን የጠቀሱት አርሶአደር ወንደሰን ከሚያለሙት አራት ሄክታር መሬት ቢያንስ 100 ኩንታል የስንዴ ምርት ለመሠብሠብ ዕቅድ ይዘው እየተንቀሳቀሱ መኾኑን ገልጸዋል።

ሌላኛው አርሶ አደር ዳኜ ዳምጠው ለስምንት ዓመታት ያህል በመስኖ ልማት ተሰማርተው በመሥራት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ከመኸር እርሻው ይልቅ በበጋ መስኖ የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ የጠቀሱት አርሶ አደር ዳኜ
በዚህ ዓመትም አራት ሄክታር መሬት ለማልማት በዝግጅት ላይ ናቸው። ለዚህም የሚኾን ከዘጠኝ ኩንታል ያላነሰ የአፈር ማዳበሪያ ቀድመው ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት ተጠቃሚ ይሁኑ እንጅ የዕለት ተዕለት ድካማቸውን የሚፈትን የውኃ መሳቢያ ጄኔሬተር እና ሸራ ለልማታቸው ትልቅ እንቅፋት ኾኖባቸዋል።

ለአብነትም 30 አርሶ አደሮች አንድን ጄኔሬተር ብቻ ተጋርተው እንዲጠቀሙ መገደዳቸውን ያነሳሉ። ባለፈው ዓመትም በእነዚህ ችግሮች ሳቢያ ለከባድ ኪሳራ መዳረጋቸውን አስታውሰዋል። በመኾኑም አርሶ አደሮቹ ለችግሮቻቸው ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የሲያደብር እና ዋዩ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጥላሁን እንዳላማው በዚሁ በጀት ዓመት ከ3 ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት መታቀዱን ገልጸዋል።

በዚህ የመስኖ ልማት ከ1 ሺህ 900 በላይ አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ። ከሚለማው መሬትም 152 ሺህ ኩንታል የስንዴ ምርት ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል።

ምርታማነቱን በሄክታር በአማካኝ 56 ኩንታል ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል። በተለይም የታቀደውን ምርት ለማግኘትም አርሶአደሮች በኩታ ገጠም እንዲያለሙ እና ሜካናይዜሽንን እንዲጠቀሙ ከማድረግ ባሻገር በቂ የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር እየተሰራጨ መኾኑን አስታውቀዋል።

አርሶ አደሮቹ ያነሱትን የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓንፕ አቅርቦት ችግር ለመፍታትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ጥረት እየተደረገ መኾኑን ጠቁመዋል።

በአማራ ክልል በ2019 በጀት ዓመት ከ734 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዷል። ከዚህም ከ95 ሚሊዮን 281 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_21_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleአዲስ አበባ የ2026 የከተሞች ዘላቂ ልማት ዓለም አቀፍ ሽልማት ተሸለመች።