#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ ርዕይ!

10
‎‎የኢትዮጵያ የታሪክ አደራ – የሀገረመንግሥት ምሥረታ ‎ኢትዮጵያ ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ የተዘረጋ ረጅም የሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ ካላቸው ጥቂት የዓለማችን ሀገራት መካከል አንዷ ናት።
ከአክሱም፣ ዛጉዌ እና ሰሎሞናውያን ሥርወ መንግሥታት ጀምሮ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በአጼ ቴዎድሮስ፣ አጼ ዮሐንስ፣ አጼ ምኒልክ እና አጼ ኃይለሥላሴ አማካኝነት የተከናወኑ የማዕከላዊ መንግሥት ማጠናከሪያ ሥራዎች ሀገሪቱ በጠንካራ መዋቅር እና በሉዓላዊነት ላይ እንድትቆም አድርገዋታል።
‎
‎የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ “የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ” በተሰኘ መጽሐፋቸው እንደገለጹት፤ ይህ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ የነፃነት እና የማንነት መገለጫ ኾኖ ያገለገለ ቢኾንም በየዘመናቱ የውስጥ አንድነት እና የፍትሐዊነት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ከመመለስ አንጻር ውሥብሥብ ፈተናዎች ነበሩበት።
‎
‎በአሁኑ ወቅት አማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ደረጃ የመንግሥት ምሥረታ እየተካሄደ ይገኛል። ‎ይህ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ምዕራፍ ታሪካዊ ቅርሶችን መሠረት ያደረገ እና አዳዲስ ሀገራዊ እውነታዎችን ያገናዘበ ለውጥ የሚጠይቅ በመኾኑ፣ አዲስ የሚመሠረተው መንግሥት ሀገሪቱን ወደተሻለ የዕድገት እና የሰላም ምዕራፍ ለማሻገር መሠረታዊ እርምጃዎችን በቁርጠኝነት መውሰድ ይኖርበታል።
‎
‎ከእነዚህም መካከል በፖለቲካ እና የታሪክ ልዩነቶች ላይ ውይይት ለማድረግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1265/2014 መሠረት ያደረገ አካታች ሀገራዊ ምክክር እና ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ማድረግ ዋነኛው ነው።
‎
‎በተጨማሪም በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 እና 79 በተደነገገው መሠረት የሕግ የበላይነትን እና የፍርድ ቤቶችን ነፃነት ማረጋገጥ፣ የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ እና ሙስናን በማያወላውል ሁኔታ መታገል የመንግሥት ቀዳሚ ግዴታ ሊኾን ይገባል።
‎
‎በሌላ በኩል የዓለም ባንክ ሪፖርቶች እና የፖሊሲ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የሕዝብ ቁጥር ዕድገትን ከኢኮኖሚ አቅም ጋር በማጣጣም ኢኮኖሚያዊ ፍትሕን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
‎
‎በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን ሪፖርቶች እንደሚያስገነዝቡት በግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው በመመለስ እና መብቶቻቸውን በማስከበር ማኅበራዊ ውህደት እና የሕዝቦች እርቅ ማውረድ እንደሚገባ ተመላክቷል።
‎
‎በጥቅሉ የኢትዮጵያ የታሪክ አደራ የሚያሳየው ጥንካሬዋ የሚመነጨው ከሕዝቦቿ ጥበብ እና ከአንድነት መኾኑን ነው። ሀገረ መንግሥት ግንባታ በአንድ ጀምበር የሚያልቅ ሳይኾን በተቋማት ጥንካሬ፣ በፍትሕ እና በዜጎች እኩልነት የሚገነባ ቀጣይነት ያለው ሂደት በመኾኑ አዲስ የሚመሠረተው መንግሥት የገባውን ቃል በተግባር ማዋል የሚጠበቅ ተግባር ነው። እርስዎስ በዚህ ጉዳይ ምን አስተያየት አለዎት? በሀሳብ መስጫው ያጋሩን
‎
‎
‎
‎ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ ርዕይ! ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የመንግሥት ሠራተኛው ሚና!
Next articleምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችን ሹመት አጸደቀ።